እንደ ጀግኖች አርበኞች ሁሉ በመከባበር እና በሀገር ፍቅር አሁን ያለውን ሀገራዊ ፈተና ማለፍ እንደሚገባ አሚኮ ያነጋገራቸው የባሕር ዳር ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

168
እንደ ጀግኖች አርበኞች ሁሉ በመከባበር እና በሀገር ፍቅር አሁን ያለውን ሀገራዊ ፈተና ማለፍ እንደሚገባ አሚኮ ያነጋገራቸው የባሕር ዳር ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 27/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ጀግኖች አባቶችና እናቶች ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ያደረጉትን ተጋድሎ የአሁኑ ትውልድ ሊማርበት እንደሚገባ አሚኮ ያነጋገራቸው የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል:: አሁን ያለው ትውልድ ኢትዮጵያ እየገጠማት ያለውን የሠላም እጦት በሰከነና በተደራጀ መልኩ መፍትሔ ሊፈልግ እንደሚገባም ነው ሀሳባቸውን የሰጡት፡፡
አቶ አሞኘ ታሪኩ በባሕር ዳር ከተማ የቀበሌ ሁለት ነዋሪ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ታፍራ እና ተከብራ የቆየችው በጥንት አርበኞች ተጋድሎ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ አሁን በኢትዮጵያ የሚሰማው ሁሉ ለእሳቸው አዲስ እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡ 65 ዓመታቸው መሆኑን የገለጹት አቶ አሞኘ በየቦታው የሚስተዋለው የሠላም እጦት እንደሚያሳስባቸው ገልጸዋል፡፡ “እኔ ከድሮ ጀምሮ ከየሀገሪቱ ጫፍ ተማሪዎች ሲመጡ እንግዳነት ይሰማቸዋል ብዬ እንደ ልጆቼ ነው የምንከባከባቸው፡፡ እኛ ድሃም ነበርን አሁን ግን ተሻሽለናል፤ ያጣነው ቢኖር ሠላም ነውና ያላስለመድነውን መበጣበጥ ማስወገድ አለብን” ሲሉ መክረዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ሠላም ሊሆኑ የሚችሉት ሲከባበሩና ሲፋቀሩ ስለሆነ ከመነካከስ የአብሮነት ባሕሉን ማዳበር ግድ እንደሚል ነው የገለጹት፡፡
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ወርቁ አያሌው ኢትዮጵያ ከምንም በፊት የሰው ልጅ የሚከበርባት ሀገር መሆን አለባት ብለዋል፡፡ የሰው ልጅ በማንነቱ ምክንያት ብቻ በየቦታው መገደል የለበትም፤ በዚህ ሁኔታም ሀገር ልትቀጥል ስለማትችል መንግሥት የሰውን ልጅ የመኖር መብቱን ሊያስከብርለት ይገባል ብለዋል፡፡
ዜጎች ሁሉ የተጋረጠባቸዉን ባይተዋር የሆነ የመጠፋፋት ድርጊት ሊጸየፉትና አንድነታቸዉን ሊጠብቁ እንደሚገባ መክረዋል፡፡ “አባቶቻችን በባሕላዊ የጦር መሣሪያ ነበር ሀገርን ከጠላት ጠብቀው ያስረከቡን፤ አሁን ግን እኛ በራሳችን በዘር፣ በጎሳ፣ እንባላለን፤ ይህ አካሄድ ስለማያዋጣን ፈጥነን ወደ አንድነታችን መመለስ ይኖርብናል” ብለዋል፡፡
ወጣት ሀብታሙ ካሴ አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ በጣም የሚያሳዝንና የሚያሳፍር እንደሆነ ነው የገለጸው፡፡ ይህን የመከራ ጊዜ ኢትዮጵያውያን ተቻችለው ካላሳለፉት በጣም የሚያስከፋ ችግር ሊያጋጥም እንደሚችል ተናግሯል፡፡ መንግሥት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሕዝብ በየቦታው በማንነቱ ብቻ የሚገደለው የአማራ ሕዝብ ጉዳይ ሊያሳስባቸው እንደሚገባም ገልጿል፡፡ በተለይ መንግሥት የዜጎችን ጩኸት ሊሰማው ይገባል፤ የሰውን ሕይወት ለማዳን መረን የለሽ ትዕግስት አያስፈልግም ያለው ወጣቱ አባቶቻችን እንደዚህ አይነት ጥላቻን አውርሰዉን አልሄዱም ብሏል፡፡ አርበኞች ባደረጉት ተጋድሎ ያስገኙትን ድል የአሁኑ ትውልድ ሊያበላሸው እንደማይገባ ነው አስተያየት የሰጠው፡፡
ተማሪ እየሩስ ጥላሁን አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው ሁኔታ በመደማመጥና በመረጋጋት መፍታት እንደሚገባ ጠቁማለች፡፡ “ኢትዮጵያ የሁላችንም ሀገር ስለሆነች ለሠላሟ ሁሉም ዜጎች እኩል ማሰብና መሥራት እንጂ አንዱ ገንቢ አንዱ አፍራሽ መሆን የለበትም፡፡ አባትና እናት አርበኞቻችን እኮ ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው ማሰብ ሳይሆን ለሀገራቸው ሉዓላዊነት ቅድሚያ ሰጥተው ነው ሕይወታቸዉን የገበሩት፡፡ ታዲያ እኛስ ለምን የራሳችንን ጥቅም ብቻ እናስቀድማለን?” ብላለች፡፡
ዘጋቢ፡- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየአባ ኮስትር በላይ ዘለቀ የጦር ስልቶች
Next articleፖለቲከኞች፣ ምሁራን እና የመገናኛ ብዙኃን ታሪክን የስሜት መቀስቀሻ ከማድረግ ተቆጥበው ለጋራ አብሮነት ታሪክ ያለውን ፋይዳ ሊያስቀድሙ እንደሚገባ የአርበኛ ልጆች እና አባቶች ተናገሩ፡፡