ʺምድር ብትጨነቅ ሠማይ ቢሰነጠቅ መች ይሸበርና የምሥራቁ መብረቅ”

265
ʺምድር ብትጨነቅ ሠማይ ቢሰነጠቅ
መች ይሸበርና የምሥራቁ መብረቅ”(በድጋሜ የቀረበ)
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 27/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ክንዳቸው ይሰብራል፣ ግንባራቸው ያስፈራል፣ ዝናቸው ያሸብራል፣ አትንኩን ነው ቃላቸው፣ አይመለሱም ከነኳቸው፡፡ ኢትዮጵያን በክፋት የረገጡ እግሮች፣ የተመለከቱ ዓይኖች፣ የተሳለቁ ጥርሶች፣ የነካኩ እጆች እድሜ የላቸውም፡፡ እንደ ጉም በነው እንደ ጭስ ተነው ይጠፋሉ እንጂ፤ ስለ ኢትዮጵያ ክብር፣ ደም ፈሷል፣ አጥንት ተከስክሷል፣ ጤዛ ተልሷል፣ መራራው ተቀምሷል፡፡ ኢትዮጵያ በየዘመናቱ የተፈነተች፣ ፈተናዋን በሚገባ ያለፈች፣ አስቀድማ የተመረጠች፣ በጥበብ የተጠበቀች፣ ለምስክርነት የተቀመጠች ሀገር ናት፡፡
ፈጣሪን የሚመስሉት፣ ሕጉን የሚተገብሩለት፣ በትዕዛዙ የሚመሩለት፣ እርሱም የሚጠብቃቸው፣ ለመከራው ቀን መጠለያ ይሆኑ ዘንድ ያስቀመጣቸው ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ የእውነት ምስክር፣ የማትመረመር ሚስጥር፣ የማታረጅ ክብር ናት፡፡ ልጆቿ ይመኩባታል፣ አብዝተው ይወዷታል፣ ለክብሯ ይሰውሏታል፣ መሪር ሞትን ይቀምሱላታል፡፡ ጠላት ቢደረደር፣ መከራው ቢጨማመር ኢትዮጵያዊያን ክንዳቸው አይዝልም፡፡
የኦጋዴን በረሃ ይጋረፋል፡፡ ምድሩ አስፈሪ ነው፡፡ በዚሕ ምድር አንድ ታላቅ ሰው ተወለዱ፡፡ የተወለዱበት ዘመንም 1871ዓ.ም ነበር፡፡ አስተዳደጋቸው በጥበብ የተመላ ነበር፡፡ ገና በለጋ እድሜያቸው ቁራዕን ቀሩ፣ ሃይማኖታዊ ትምህርቱን በሚገባ ተከታተሉ፡፡ የሀገራቸውን ጉዳይ ባነሱ ጊዜ ወኔ ይመጣባቸዋል፡፡ በተለይም በወጣነት ዘመናቸው ኢትዮጵያዊያን በዓድዋ ላይ የፈፀሙት ጀብዱ ያስደንቃቸው ነበር፡፡ እሳቸውም ያን አይነት ጀብዱ የመፈፀም ዕድል ያገኙ ዘንድ ሳይመኙ አልቀሩም፡፡ ጀግኖችን ባስታወሱ ቁጥር ይኩራሉ ይሏቸዋል፡፡ ከጀግኖች ምድር በመፈጠሬ እኮራለሁ ይሉም ነበር ይባላል፡፡ ሀገራቸው ኢትዮጵያን እነካሁ የሚለውን ሁሉ አይቀጡ ቅጣት ለመቅጣት በዝግጁነት መቀመጥ ጀመሩ የምሥራቁ መብረቅ ዑመር ሰመተር፡፡
ዑመር ሰመተር በኦጋዴን ካልካዩ በተባለ ሥፍራ ተወለዱ። አስተዳደጋቸው በጥበብና በጀግንነት የተመላ ነበርና ሕዝብና ሀገር የማገልገል ሥራቸውን በወጣነት ዘመናቸው ነበር የተቀላቀሉት፡፡ ደጅ አዝማች ዑመር ሰመተር የኤልቡር ገዢ ሆኑ፡፡ ጣልያን 40 ዓመታት ተዘጋጅታ ዳግም የጠብ ድግስ የደገሰችበት ዘመን ደርሷል፡፡ ዙሪያውን እየዞረች ነገር ትፍልጋለች፡፡ በዘመኑ ኃያል ነን የሚሉ የአውሮፓ ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ ይመክሩና ይዘክሩ ጀምረዋል፡፡ የዓድዋ ጀግኖች የተወለዱባት፣ ጀግኖች የሚፈጠሩባት መሆኗን አላወቁም ነበርና ጠብ አጫሪነታቸውን ቀጠሉ፡፡ ኢትዮጵያም የጦርነት ዘመን ያበቃ ዘንድ ለፍቅር እጇን ዘረጋች፡፡ ስለ ፍቅር ሁሉንም አስቀደመች፡፡ በክብሯ የሚመጣ ቢኖር ግን እንደማትመርው አስቀድማ ታውቃለች፡፡
1928ዓ.ም ደረሰ፡፡ የ40 ዓመቱ የጣልያን ድግስ ይበላ ጀመር፡፡ የእሳቱን አጥር አልፋ የኢትዮጵያን ግዛት ረገጠች፡፡ ከድግሱ በፊት ጀግኖች ለፍቅር እጅ ነሡ፡፡ ፍቅር አይሆንም ብሎ ሀገራቸውንና ክብራቸውን ለደፈረው የማይቀረውን ነፍጥ አነሱ፡፡ ውጊያው ተጀመረ፡፡ ኢትዮጵያዊያን በየአቅጣጫው ለእናት ሀገራቸው ይዋደቁ ጀመር፡፡
በዚህ ዘመን ለእናት ሀገራቸው ተጋድሎ ካደረጉ ኢትጵያዊያን አርበኞች ደጅ አዝማች ዑመር ሰመተር አንደኛው ናቸው፡፡ ጀግንነታቸው ከወረራው አስቀድሞ በነበረው ጊዜ ነው የጀመረው፡፡ የእንግሊዝ መንግሥትና የኢትዮጵያ መንግሥት በሶማሊያና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ወሰን ለማካለል ስምምንት አድርገው ነበር፡፡ ከእንግሊዝ መንግሥት ወገን ኮሎኔል ክሊፎርድ ከኢትዮጵያ መንግሥት ወገን ፊታውራሪ ተሰማ ባንቴ ዋና ወሰን ተካላዮች ሆነው በኦጋዴን ውስጥ በወልወል በኩል አልፈው የሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች ከብቶቻቸውን የሚያግጡበትንና ውኃ የሚያጠጡበትን ለመርመር አለፉ፡፡ በዚያ በኩል ሲያልፉም ካፒቴን ቺማሩታ የሚባለው የኢጣሊያ ተወላጅ ʺዱባት” የተሰኙትን የሶማሊያ ወታደሮች ይዞ ስምምነት የተደረገበትን ወሰን አልፎ መተላለፊያ ከለከለ፡፡
ኢትዮጵያዊያን ጠብ አጫሪነቱን እንዲያቆም ጠየቁት፡፡ አሻፈረኝ አለ፡፡ ወሰን የሚካለሉትን አደጋ እንዳይደርስባቸው ይጠበቁ በነበሩ በፊታውራሪ ሺፈራውና በፊታውራሪ ዓለማየሁ ላይ ድንገት አደጋ ጣለ፡፡ በአውሮፕላን የታገዘ ውጊያ ጀመረ፡፡ ለፍቅር የሄዱት ኢትዮጵያዊያን ያልጠበቁት ቢገጥማቸውም በጀግንነት ሲፋለሙ ዋሉ፡፡ ጀግኖች ተዋደቁ፡፡ ኢጣሊያ በዚህ አላበቃችም ለኢትዮጵያ ጥያቄ አቀረበች፡፡ ለተጎዳባት ወታደር ኢትዮጵያ ካሳ እንድትከፍል፣ ደጅ አዝማች ዑመር ሰመተር ለኢጣሊያ እንዲሰጡ፣ ፊታውራሪ ሽፈራው ከሹመታቸው እንዲሻሩ፣ ደጅ አዝማች ገብረማርያም ወልወል ድረስ ሄደው ይቅርታ እንዲጠይቁ ጠየቀች፡፡
ጉዳዩን ለዓለም አሰራጨች፡፡ ኢትዮጵያም ነገሩ ሁሉ በሰላም እንዲፈፀም ጥረት ማድረጓን ቀጠለች፡፡ ኢጣሊያ ግን ጠብ አጫሪነቷን ቀጠለች፡፡ የንቀታቸው ጥግ የሚገርም ነበር፡፡ የኦጋዴኑ መብረቅ እንዴት እጁን ይሰጣል፡፡ ደጅ አዝማች ዑመር ሰመተር በለጋ እድሜያቸው ሲሹት የነበረው ለሀገር ጀብዱ የመፈፀም ዘመን ደርሷል፡፡ ጦርነቱም ቀጠለ፡፡ ደጅ አዝማች ዑመር ሰመተር እጅ ይስጥ የሚለውን በሰሙ ገዜ ʺከአገሬ አፈር የሚደባልቅ ቤልጅግና ጎራዴ ይዤ እንጂ ጫት ተሸክሜ የምመጣ እንዳይመስልህ” የሚል ቆፍጣና መልዕክት ላኩ ይባላል፡፡
በቆራሔ በኩል ከደጅ አዝማች አፈወርቅ ጋር አያሌ ጀብዱ ፈፀሙ፡፡ ሀገራቸውን ለመድፈር የመጣውን የጣልያን ሠራዊት በጀግንነት ይፈጁት ጀመር፡፡ በአየር በምድር እየተደበደቡ ከምሽግ አልወጣም አሉ፡፡ በአንድ ወቅት በጣሊያን ስድሰት ባታሊዮን ተከበቡ፡፡ የከፋ ጉዳት የማያስደርስ ስልት፣ ምሽግ የሚደረምስ ጀግንነት ያስፈልጋቸው ነበር፡፡ በሁለቱም የተካኑት የኦጋዴኑ መብረቅ በዙሪያቸው የነበረው የጠላት ሠራዊት እንደ ጭስ በትነው ከከበባ ወጡ፡፡ ድልም መቱት፡፡
ʺምድር ብትጨነቅ ሠማይ ቢሰነጠቅ
መች ይሸበርና የምሥራቁ መብረቅ”
የኢጣሊያ ጦር ኢትዮጵን ሲወር ንጉሠ ነገሥት ቀደማዊ ኃይለ ስላሴ ወደ ጅግጅጋ በማቅናት በዚያ የሚገኘውን ሠራዊት አበራታቱ፡፡ ʺ…. ሰው ለዘላላም ነዋሪ ሊሆን አልተፈጠረም፤ በመጨረሻም ከዓለም የሚለየው ሞት ነው፡፡ ይህ ሞት ይቀድማል፣ ይከተላል፣ እንጂ ለሰው ልጅ ሁሉ አይቀርለትም፡፡ ከመቃብር በላይ እየሰፈፈ የሚታይ ዓለም እስኪያልፍ ድረስ መታሰቢያ ሆኖ የሞኖር ስም ነው፡፡ የዛሬ 40 ዓመት በዓድዋ ይህ ጠላታችን በተዋጋን ጊዜ የኢትዮጵያ ጀግኖች ድል ስለመቱት፣ እንኳንስ በሕይወት ያላችሁት በዚያውም የቀሩት ቢሆኑ ስማቸው ሳይረሳ ለዘለዓለም ሲጠራ ይኖራል፡፡ አሁንም ላለው ትውልድ ዋና የሚያኮራ ነው፡፡ ደግሞ ወንድ ልጅ እንኳንስ አገሩንና ርስቱን የሚቀማ ወገኑን ወደ ስደት የሚያደርስ ጠላት ተነስቶበት እንዲያውም ቢሆን ዋና ምኞቱና የሚያኮራው ሞት በጦርነት የሚደርስበት ነው፡፡ ዶሮ እንኳን ጫጩቶቿን ካሞራ ለማዳን ትተናነቃለች፡፡ ይህ ከሆነ በአእምሮም በጉልበትም ብዙ ሺህ ጊዜ የሚበልጠው ሰው ምን ያኽል ከጠላት ጋር መታገል እንደሚገባው እወቁ፡፡ እንግዲህ ለሰው ልጅ ሞት በመጨረሻው የማይቀርለት ከሆነ የማይጠፋ ስሙን ለመትከል አሮጌ (ያረጁ) አባትና እናቱን፣ ሚስቱ ልጆቹ እንዳይሰደዱበትና ዛሬ በነጻ አገራቸው በኢትዮጵያ ከብረው ሲኖሩ ነፃነት ያጡ እንደ ሆነ ይህ ክብራቸው ቀርቶ በውርደት እንዳይወድቁ ለማድረግ የመጣውን ጠላት በመውጋት ሕይወታችሁን ብታሳልፉ ክብራችሁ የቱን ያክል ይሆን? የከበረ ስማችሁም በልጆቻችሁና በወገኖቻችሁ ዘንድ ሲመሰገንና በዓለም ታሪክ ሲጠራ ይኖራል፡፡….” አሉ፡፡
ተጋድሎው ቀጠለ፡፡ እነ ደጅ አዝማች ዑመር ሰመተር እና ሌሎች ጀግኖች በተሰለፉበት የምሥራቁ ንፍቅ የጣልያን ወታደር ኃይል ይጨመረኝ እያለ ይጣራ ጀመር፡፡ በዚያ በረሃ ሳይቀምሱ እንጀራ ሳይጠጡ ውኃ እያለሙ እየተኮሱ እጅ ያስነሱ ጀመር፡፡ ደጅ አዝማች ዑመር የጥርሳቸው ንጣት፣ የልባቸው ኩራት፣ የተሰጣቸው ድፈረት አጀብ ያሰኛል ይሏቸዋል፡፡ የኦጋዴኑ የበረሀው መብረቅ ዑመር ሰመተር ግንባራቸው ይፋጅ ነበር፡፡
መብረቁ ደጅ አዘማች በቆራሔ ከጠላት ምሽግ የጨበጣ ውጊያ በማካሄድ ታላቅ ጀበዱ ፈጸመዋል፡፡ በሀፍዱግ፣ በሀነሌላ በተለያዩ የኦጋዴን በረሃዎች አያሌ ጀብዱዎችን ፈፀሙ፡፡ እኒህ ታላቅ ሰው በጉርለጉቤው ጦርነት በጣላት ጥይት ተመቱ፡፡
ከቁለስላቸው ያገገሙ ዘንድም ሀርጌሳ ከዛም በኬንያ በኩል ተጉዘው ወደ ሎንደን አቀኑ፡፡ ህመሙ አልተሻላቸውም፡፡ ይልቁንም ያ የመጨረሻው እጣ ደረሰ፡፡ ሕይታቸው አለፈች፡፡ እኒህ ጀግና ያለፉበት አያሌ ጀብዱዎችን ፈፅመው ያለፉት መጋቢት 6 ቀን 1936ዓ.ም ነበር፡፡ ታላቁ የጦር መሪ ኢትዮጵያዊያን አንድ ሆነው በአንድ ሰንደቅ ሥር እንዲሆኑ ምኞታቸውና ሥራቸው የነበር ናቸው፡፡ ባሕል፣ ወግና ሃይማኖት አንደኛውን ሊያራርቁ የሚችሉ አለመሆናቸውንም ይናገሩ ነበር ይባላል፡፡ በሞታቸው ጊዜም እንዲህ ሲሉ ተቀኙላቸው፡፡
ʺተጋዳይ እወልወል እጠረፉ ዳር
ተጋዳይ አፍዱግ እጠረፉ ዳር
ተጋዳይ ቆራሔ እጠረፉ ዳር
ተጋዳይ ሀነሌ እጠረፉ ዳር
የመትረየሱ ሼክ የለበን መምህር
ሞት ጠራህ አንተንም ዑመር ሰመተር” መብረቁ ደጅ አዝማች አንድነት፣ ኢትዮጵያዊነትና አይበገሬነት ሀብታቸው ነበር፡፡ የእሳቸው ሀብትም ለዛሬዎቹ ኢትዮጵያዊያን ውርስ ይሆናል፡፡ ክብር ለጀግኖች፣ ኢትዮጵያ እንድትኮራ፣ ስሟ በክብር እንዲጠራ፣ በኃያላኑ ፊት እንደትፈራ ላደረጉ፡፡
የኢትዮጵያ ታሪክ ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀደማዊ ኃይለ ሥላሴ በተክለ ጻዲቅ መኩሪያን ተጠቅሜያለሁ፡፡
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleʺሀገርህን ከወደድካት ወታደር ሁንላት”
Next articleየአባ ኮስትር በላይ ዘለቀ የጦር ስልቶች