
የሚጠቅማቸውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 26/2013 ዓ.ም (አሚኮ) መጪው ሀገራዊ ምርጫ ግንቦት 28/2013 ዓ.ም ይካሄዳል፡፡ በመሆኑም መራጮች ይበጀኛል የሚሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ የምርጫ ካርድ በማውጣት ላይ ናቸው፡፡ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ መሰረት ጭማሪ ሁለት ሳምንታት ተሰጥቶ የምርጫ ካርድ ያላወጡ ዜጎችም ጊዜአቸውን ተጠቅመው የምርጫ ካርዳቸዉን እያወጡ ነው፡፡ በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የሚገኙ አርሶ አደሮችም የግብርና ሥራቸውን ከማከናወን ጎን ለጎን የምርጫ ካርዳቸውን እየወሰዱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
አርሶ አደር እንግዳው ታደሰ በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አየሁ ጓጉሳ ወረዳ ነዋሪ ናቸው፡፡ ለስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ በእጃቸው አስገብተዋል፡፡ ምርጫው ሠላማዊ እንዲሆን የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡም አቶ እንግዳው ተናግረዋል፡፡ ዕጩ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርጉትን የምረጡኝ ቅስቀሳ በራዲዮ እየተከታተሉ እንደሚገኙም አስረድተዋል፡፡
በተለይም የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ አማራጭ ሃሳቦችን የሚያቀርቡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ልዩ ትኩረት ሰጥተው እየተከታተሉ መሆናቸውን ነው አርሶ አደሩ የተናገሩት፡፡
አርሶ አደር ደሳለው በላይ ደግሞ የአንከሻ ጓጉሳ ወረዳ ነዋሪ ናቸው፡፡ በግብርና ዘርፍ በግብርናው ዘርፍ ተሻለ ቴክኖሎጂ ለማምጣት የሚቀርቡ መረጃዎችን እየተከታተሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የሚጠቅማቸውን ፓርቲ ለመምረጥ ይችሉ ዘንድም የመራጭነት ካርድ በአቅራቢያቸው ከሚገኝ የምርጫ ጣቢያ አውጥተዋል፡፡
የዳንግላ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር አምሳሉ መንግሥቴ የአርሶ አደሮችን ጥቅም የሚያስጠብቅ፣ ሀገራዊ ሠላምን የሚያስከብር፣ የሀገር ሉዓላዊነትን የሚያስጠብቅና ለወጣት ልጆቻቸው የሥራ ዕድል የሚፈጥር የፖለቲካ ፓርቲን ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ