በኢንቨስትመንት ስም ታጥሮ የተቀመጠው ቦታ ከ58 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ አድርሷል፡፡

402

በኢንቨስትመንት ስም ታጥሮ የተቀመጠው ቦታ ከ58 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ አድርሷል፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 25/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የፌዴራል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ለልማት በሚል በ2008 ዓ.ም
ነበር በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አረርቲ ከተማ 150 ሄክታር መሬት ከአርሶ አደሮች ነጻ ያደረገው፡፡ ለዚህም 165 አርሶ አደሮች ተነሺ
መኾናቸውን የወረዳው ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡ 100 ሄክታሩ በግል ቀሪው ደግሞ በመንግሥት
እንዲለማ ነበር የታቀደው፡፡ የጽሕፈት ቤቱ ኀላፊ አብርሃም ፈለቅ እንደተናገሩት በግል እንዲለማ ከሚፈለገው መሬት ውስጥ
የለማው 30 ሄክታር ብቻ ነው፡፡
በመንግሥት ሊለማ የታሰበውም በተገቢው መንገድ እንኳን አልታጠረም፡፡ አቶ አብርሃም እንዳሉት ለኢንዱስትሪ ፓርኩ
ከተከለለው 150 ሄክታር መሬት 120 ሄክታሩ እስካሁን ጥቅም ላይ አልዋለም፡፡ ለዚህም የኤሌክትሪክ መሠረተልማት አቅርቦት
ችግር በመሠረታዊነት ይነሳል፡፡
ወረዳው በማኛ ጤፍና በአረርቲ ሽምብራ የሚታወቅ ነው፡፡ ለኢንዱስትሪ በተከለለው ቦታ አካባቢ ጤፍ፣ ሰንዴ፣ ሽንኩርት እና
ሽምብራ በስፋት ይመረታል፡፡ ከአንድ ሄክታር መሬት በአማካኝ እስከ 25 ኩንታል ጤፍ እንደሚመረት የወረዳው ግብርና ጽሕፈት
ቤት ኀላፊ ናትናኤል ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡ 120 ሄክታር መሬቱ በዓመት 3 ሺህ ኩንታል ጤፍ ይመረትበታል ማለት ነው፡፡ በዚህ
ስሌት መሠረት ለአምስት ዓመታ ያለምንም ጥቅም የተቀመጠው መሬት በአማካኝ 15 ሺህ ኩንታል ገደማ ጤፍ ማምረት
የሚያስችል ነው፡፡ ታጥሮ የተቀመተው ቦታ ለጤፍ ልማት ውሎ ቢሆን መንግሥት ባወጣው የጤፍ መሸጫ ተመን መሠረት እስከ
58 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር ገደማ የሚያስገኝ ነበር፡፡
በሌላ በኩል በአንድ ሄክታር መሬት ላይ እስከ 40 ኩንታል ስንዴ ያመረታል፡፡ ስለዚህ በአምስት ዓመታቱ 24 ሺህ ኩንታል ገደማ
ስንዴ ማምረት የሚያስችል መሬት ጦሙን አድሯል ማለት ነው፡፡ በሄክታር 360 ኩንታል ገደማ ሽንኩርት የሚመረት ሲሆን በዓመት
43 ሺህ 200 ኩንታል ሽንኩርት እንዲሁም በአምስት ዓመታቱ 216 ሺህ ኩንታል ሽንኩርት ያለምንም ሥራ ከተቀመጠው መሬት
ማግኘት ያስችላል፡፡ መሬቱ በክረምት ከሚመረትበት ሰብል በተጨማሪ በመስኖ በአትክልትና ፍራፍሬ ማልማት እንደሚቻል
የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ናትናኤል ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ያለምንም ጥቅም መቀመጡ ትክክል
እንዳልኾነ የወረዳው አስተዳደር እና ማኅበረሰቡ በተደጋጋሚ ቢገልጹም ውጤት አለመገኘቱን ነው የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት
ጽሕፈት ቤት ኀላፊው ያስታወቁት፡፡
የፌዴራል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጥያቄው ተገቢ መሆኑን ገልጿል፡፡ ይሁን እንጂ ለኢንዱስትሪ ፓርኩ መሬትን
ከሦስተኛ ወገን ነጻ ማድረግ ትልቅ ስኬት መሆኑን ነው የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሳንዶቃን ደበበ የተናገሩት፡፡ ሁሉም ነገር
መሬት ከማግኘት ይጀምራል ያሉት ሥራ አስፈጻሚው ቀጥሎ ገንዘብ ስለማፈላለግ፣ ስለግንባታ እና ባለሀብቶችን ስለመሳብ
ይታሰባል ብለዋል፡፡
መሬት ይዞ ባለሀብት ማፈላለግ ያለመሬት ባለሀብትን ከመጠበቅ እንደሚለይም አንስተዋል፡፡ ከአረርቲ በተጨማሪ ሌሎች ለፓርክ
ዲዛይን የተደረጉ ከ10 በላይ አካባቢዎችም ለረጅም ጊዜ ታጥረው መቀመጣቸውን አብራርተዋል፡፡ አቶ ሳንዶቃን አካባቢዎቹን
ለማልማትም በቀጣይ የሚሠሩ ብዙ ተግባራት መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ በተለይ ተገንብተው ለተጠናቀቁ ሸዶች የኀይል
አቅርቦትን በማሟላት ባለሀብቶችን ለመሳብ እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ይህ በመንግሥት አቅም ብቻ ውጤታማ ሊሆን
ስለማይችል የባለሀብቶች ተሳትፎ ሊጨመርበት እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

Previous article“ትህነግና የጥፋት የበኩር ልጁ ኦነግ-ሸኔ በሽብርተኝነት ለመፈረጅ የውሳኔ ሃሳብ መቅረቡ የሕዝብ ትግል እያሸነፈ ስለመሆኑ ምልክት ነው” የአማራ ብልጽግና ፓርቲ
Next article“የሀገር ጠላቶችን ለማሸነፍ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ሊቆሙ ይገባል” ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን