
- የትንሣኤን በዓል በመተሳሰብና የተቸገሩትን በመርዳት ለማክበር መዘጋጀታቸውን በወልቃይት ጠገዴ የሰቲት ሁመራ ከተማ
ነዎሪዎች ገለፁ።
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 23/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በክርስትና እምነት ተከታዮች በፆም፣ በፀሎት እና በስግደት ሲከበር የቆየው
የዐቢይ ፆም በነገው እለት በዓለ ፋሲካው ይሆናል። ፆሙ እየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሲል መከራን የተቀበለበትና ለሰው ልጆች
ፍቅር ሲል ራሱን ለሞት አሳልፎ የሰጠበት በመሆኑ በመተሳሰብና በፍቅር የሚከበር በዓል ነው።
በወልቃይት ጠገዴ የሰቲት ሁመራ ነዎሪዎችም የትንሣኤ በዓልን በመተሳሰብና የተቸገሩትን በመርዳት ለማሳለፍ መዘጋጀታቸውን
ተናግረዋል።
በሁመራ ከተማ የደብረ ምህረት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን አገልጋይ ዲያቆን ሳሙኤል ሙሴ “የትንሣኤን በዓልን ስናከብር
የተቸገሩትን ለመርዳት ከሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች እና ከሰበካ ጉባኤ ጋር በመሆን ከአምስት ሽህ ብር በላይ አሰባስበናል፤
በትንሣኤ ዕለትም እናቶች ከየቤታቸው እንጀራ ያመጣሉ፤ ያሰባሰብነውን ብር ደግሞ በግ ወይም ፍየል በመግዛት የተቸገሩ
ወገኖችን በማብላት በዓሉን እናከብራለን” ነው ያለው።
ዲያቆን ሳሙኤል የትንሣኤ በዓል በሰላም እንዲከበር ኅብረተሰቡ ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን አካባቢውን መጠበቅና የከተማዋን
ሰላማዊ እንቅስቃሴ ማስቀጠል ይገባል ብሏል።
ቄስ ኪሮስ ገብረ ትንሣኤ በበኩላቸው ቅዳም ስዑር ማለት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መነሳት ቀድመን የምናበስርበት ዕለት
ነው፤ ለዚህም ካህናቱ ልብሰ ተክህኗቸውን ለብሰው ቃላዋዲ እና ግጫ ይዘው በየቤቱ እየዞሩ ያድላሉ ነው ያሉት።
ቄስ ኪሮስ ገብረ ትንሣኤ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሞትን ድል ነስቶ የሐጢያት ደብዳቤችን የቀደደልንን የእየሱስ ክርስቶስን በዓል
ስናከብር በመተሳሰብ፣ የተቸገሩትን በመርዳትና የታሰሩትን በመጠየቅ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል ።
ዘጋቢ:– ያየህ ፈንቴ –ሁመራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m