
ሰበር ዜና
“የሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት)” እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት ተሰየሙ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በጉዳዩ ላይ ያወጣው መግለጫ ቀጥሎ ይቀርባል።
ባለፉት 3 ዓመታት በኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ እና የመብት መከበር ጥያቄዎች እና ትግል አማካኝነት የመጣውን ለውጥ
ለመቀልበስ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ሲፈጸሙ የቆዩ መሆኑ ይታወሳል።
በዚህም ምክንያትም የበርካታ ዜጎች ሕይወት ጠፍቷል፣ አካላቸው ጎድሏል እንዲሁም ንብረታቸው ወድሟል፤ ከቀዬአቸውም ተፈናቅለዋል።
እነዚህ ጥቃቶች ኅብረተሰቡ ቀጣይነት ባለው ሥጋት እና ፍርሐት ውስጥ እንዲኖር በማድረግ በመንግሥት ላይ እምነት እንዲያጣ፣ ዜጎች
እርስ በእርስ እንዳይተማመኑ አድርጓል። ይህ ሁሉ የሀገረ መንግሥቱን ህልውና አደጋ ላይ ለመጣል ታቅደው ሲፈጸሙ የነበሩ
መሆናቸውን ከተለያዩ ማስረጃዎች ለመረዳት ተችሏል።
ከጥቃቶቹ ከጀርባ የፖለቲካ አስተሳሰብን መነሻ በማድረግ እና የፖለቲካ ዓላማን ወይም ግብን ለማሳካት በማሰብ በንጹሐን ዜጎች እና በሕዝብ መሠረተ ልማቶች ላይ ሲፈጸሙ የቆዩ ናቸው።
በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ሲፈጸሙ የቆዩት እነዚህ ጥቃቶች የተለያዩ ፈጻሚ አካላት ነበሯቸው። ከጥቃቶቹ ጀርባ ግን በዕቅድ፤ በገንዘብ፣ በሐሳብ እና በሰው ኃይል ሥልጠና
በመደገፍ፤ የሚዲያ ሽፋን እና እገዛ በመስጠት ረገድ የመሪነት ሚናውን ሲጫወቱ የነበሩ ቡድኖች አሉ።
ኢትዮጵያን የማመሰቃቀል፤ የማዳከም እና የማፍረስ ፍላጎት ያላቸው የውጭ ኃይሎች እነዚህን ቡድኖች በቅጥረኝነት እየተጠቀሙባቸው እንድሆነም ግልጽ ነው።
የጥፋት ኀይሎቹ ሲፈጸሙና ሲያስፈጽሙ የቆዩዋቸው የጥፋት ተግባራት የሽብር ወንጀል ተግባራት ናቸው። ተግባራቱ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣው ዐዋጁ 1176/2012 አንቀጽ 3 ሥር ስለሽብር የወንጀል ድርጊት የተሰጠውን ትርጓሜ ሙሉ በሙሉ የሚያሟሉ ተግባራት እንደሆኑ መገንዘብ ተችሏል።
የሽብር ተግባራቱን የፈጽሙ ድርጅቶች
አባላትና እና ደጋፊዎቻቸውን እንደ ግለሰብ በተናጠል በሽብር ወንጀል ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ ድርጅቶቹን የሽብርተኛ ድርጅት
አድርጎ በመሰየም በሕጉ በተቀመጠው አግባብ የሽብር ወንጀል ድርጊትን በተሻለ ሁኔታ ለመቆጣጠር እና ለመከላከል ይችላል።
ስለዚህ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣው ዐዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 18 እና 19 መሠረት “ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት)” እና “ሸኔ” የሽብር ወንጀልን ዓላማቸው አድርገው የሚንቀሳቀሱ በመሆኑና የድርጅቶቹ የሥራ
አመራር ወይም ወሳኔ ሰጭ አካላት ወንጀሉን አምነው የተቀበሉት ወይም አፈጻጸሙን እየመሩት በመሆኑ፤ የሽብር ተግባር
መፈጸምም የድርጅቶቹ ጠቅላላ መገለጫ በመሆኑ፤ ድርጅቶቹ በሽብርተኛ ድርጅትነት እንዲሰየሙ የውሳኔ ሐሳብ ቀርቧል።
እንዲሁም የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣው ዐዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 23 መሠረት በተመሳሳይ
ተግባር በተሰማሩ እና በዚህ ውሳኔ ሐሳብ መሠረት ከተሰየሙት የሽብርተኛ ድርጅቶች ጋር ትብብር፤ ትሥሥር ወይም የሐሳብ
እና የተግባር ዝምድና ያላቸው ድርጅቶችና ግለሰቦች ላይም ይህ ውሳኔ ሐሳብ ተፈጻሚ ይሆናል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት
ሚያዚያ 23/2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ