በበዓል ወቅት ሊፈጸሙ ከሚችሉ የወንጀል ድርጊቶችና የተለያዩ አደጋዎች ራስን መጠበቅ እንደሚገባ የአማራ ክልል ፓሊስ ኮሚሽን አሳሰበ።

184

በበዓል ወቅት ሊፈጸሙ ከሚችሉ የወንጀል ድርጊቶችና የተለያዩ አደጋዎች ራስን መጠበቅ እንደሚገባ የአማራ ክልል ፓሊስ
ኮሚሽን አሳሰበ።
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 23/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ቀደም ባሉት በዓላት ከጥንቃቄ ጉድለት የተነሳ የስርቆት፣ የትራፊክ አደጋ፣ የእሳት
አደጋና ሌሎች ድርጊቶች እንደሚከሰቱ አሚኮ ያነጋገራቸው የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ያስታውሳሉ።
የአጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ነዋሪ አቶ አራጋው ገድፍ በበዓላት ጊዜ ከመጠን በላይ በመጠጣት በስካር መንፈስ ግጭት ይፈጠር
እንደነበር አስታውሰዋል። በበዓል ወቅት የከብት ስርቆት ሙከራ ተደርጎ በኅብረተሰቡ ጥረት ማስቀረት መቻሉንም ነግረውናል።
በበዓል ዋዜማ በሚደረግ የምግብ ዝግጁት ከጥንቃቄ ጉድለት የእሳት አደጋ እንደሚከሰት የተናገሩት ደግሞ ሌላዋ የሽንብጥ
ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አስናቁ ናቸው።
ለትንሳዔ በዓል በብዛት ሌሊት ላይ የመግደፊያ ምግብ ይዘጋጃል። በዚህ ጊዜ በመዘናጋትም ይሁን በእንቅልፍ ችግር የእሳት አደጋ
እንዳይከሰት ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
በበዓል ወቅት ሊፈጸሙ ከሚችሉ የወንጀል ድርጊቶችና የተለያዩ አደጋዎች ራስን መጠበቅ እንደሚገባ ያሳሰበው ደግሞ የአማራ
ክልል ፓሊስ ኮሚሽን ነው።
በኮሚሽኑ የማኅበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ጀማል መኮንን እንዳሉት ከበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ የተለያዩ
የስርቆት ወንጀሎች፣ ሀሰተኛ የገንዘብ ኖትን ተጠቅሞ ግብይት መፈጸም፣ ማታለል፣ ማጭበርበርና ሌሎች የወንጀል ድርጊቶች
ይፈጸማሉ፡፡ ከመጠን በላይ አልኮል ወስዶ በስካር መንፈስ የትራፊክ አደጋ ማድረስም ሌላው ችግር እንደሆነ አንስተዋል።
በሌላ በኩል በሌሊት የምግብ ዝግጂት ጊዜ በእንቅልፍ ወይንም በጥንቃቄ ጉድለት የእሳት አደጋ ሲያጋጥም እንደሚስተዋል
ጠቅሰዋል።
ፖሊስ ኮሚሽኑ በዓሉን መሠረት አድርገው ሊፈጠሩ የሚችሉ ወንጀሎችንና አደጋዎችን ለመከላከል ዝግጅት ማድረጉን
አስታውቀዋል፡፡
ማኅበረሰቡም ራሱን ከወንጀል ከማራቅ ጀምሮ ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት፡፡
በዓሉ በሰላም እንዲያልፍ የራስን፣ የቤተሰብን እና የማኅበረሰቡን ደኅንነት መጠበቅ የሁሉም ግዴታ ነው ብለዋል ኮማንደሩ።
ኀብረተሰቡ በወንጀል የሚሳተፉ አካላትን ሲመለከት ለጸጥታ አካላት ጥቆማ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡-ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleበአጣዬና አካባቢው በተፈፀመው ወንጀል ተጠያቂ የሚሆኑ አካላትን ለፍርድ እንደሚያቀርብ ኮማንድ ፖስቱ አስታወቀ፡፡
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለክርስትና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።