በአጣዬና አካባቢው በተፈፀመው ወንጀል ተጠያቂ የሚሆኑ አካላትን ለፍርድ እንደሚያቀርብ ኮማንድ ፖስቱ አስታወቀ፡፡

254
በአጣዬና አካባቢው በተፈፀመው ወንጀል ተጠያቂ የሚሆኑ አካላትን ለፍርድ እንደሚያቀርብ ኮማንድ ፖስቱ አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዚያ 22/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖች በነበረው የጸጥታ ችግር በወንጀሉ ተጠያቂ የሚሆኑ አካላትን በመለየት ለፍርድ እንደሚያቀርብ በአካባቢው የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት አስታወቋል።
የኮማንድ ፖስቱ አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል ደስታ አቢቼ የጸጥታ ሃይሉ በአካባቢው የነበረውን የጸጥታ ችግር ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለስ በትኩረት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
ኮማንድ ፖስቱ በነበረው ችግር ተዘግቶ የነበረውን መንገድ በማስከፈት የተቋረጡ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አስተዳደራዊ ሥራዎች እንዲጀመሩ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አብራርተዋል።
የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀዬአቸው የመመለስና በወንጀሉ መጠየቅ ያለባቸውን አካላት በመለየት በሕግ ተጠያቂ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ሌተናል ጄኔራል ደስታ ተናግረዋል።
ኮማንድ ፖስቱ ከተቋቋመ በኋላ በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት እየተፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
“በአካባቢው መረጋጋት በመፈጠሩ የትራንስፖርት አገልግሎቶችና ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ጀምረዋል” ብለዋል።
የስልክ፣ የውኃና የኤሌክትሪክ አገልግሎት መጀመሩንም ሌተናል ጄኔራል ደስታ ጨምረው ተናግረዋል።
በአካባቢው በተፈጠረው የጸጥታ ችግር በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በሕግ ተጠያቂ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ የአካባቢው ማኅበረሰብም አጥፊዎችን የማጋለጥና መረጃ የመስጠት ሥራ እያከናወነ መሆኑን አመላክተዋል።
“በችግሩ ላይ የሀገር ውስጥና የውጭ አካላት፣ አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶችና በመንግሥት መዋቅር ስር ያሉ አንዳንድ የሥራ ኀላፊዎች እጅ እንዳለበት ደርሰንበታል” ያሉት ሌተናል ጄኔራል ደስታ፤ በማስረጃ የተደገፉ መረጃዎች የማሰባሰብ ሥራ እንደሚሠራ ገልጸዋል። ለችግሩ መንስኤ እና ተሳታፊ የሆኑ አካላት ከሕግ ተጠያቂነት እንደማያመልጡ ተናግረዋል፡፡ ኢዜአ እንደዘገበው በጸጥታ ችግሩ የተሳተፉትን ኮማንድ ፖስቱ ጥልቅ ምርመራ በማድረግ ማስረጃ አደራጅቶ ሕግ ፊት እንደሚያቀርባቸው አረጋግጠዋል።
በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት ግዳጅ ላይ ተሰማርቶ የሚገኘው የልዩ ዘመቻ 3ኛ አየር ወለድ ብርጌድ ሻለቃ አመራር በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት መኖሩን ተናግረዋል።
በደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ሸዋ ዞንና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር በሚገኙ ዘጠኝ ወረዳዎችና አምስት ከተሞች ኮማንድ ፖስት መቋቋሙ የሚታወስ ነው።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleʺእነሆ የአላፊው ዓለም ጉዟቸውን ፈፀሙ”
Next articleበበዓል ወቅት ሊፈጸሙ ከሚችሉ የወንጀል ድርጊቶችና የተለያዩ አደጋዎች ራስን መጠበቅ እንደሚገባ የአማራ ክልል ፓሊስ ኮሚሽን አሳሰበ።