
“ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መባባስ ምክንያት አንሁን” ዶክተር ሊያ ታደሰ
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 22/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ የስቅለትና የትንሣኤ በዓላትን በማስመልከት መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ ሚኒስትሯ የስቅለትና ትንሣኤ በዓላት የሰላም፣ የደስታ እና የጤና እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡
በመልእክታቸውም “የኮሮና ቫይረስ ዋነኛ የሕዝባችን የጤና ስጋት ሆኖ ቀጥሏል” ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የኮሮናቫይረስ ምርመራ ከሚደረግላቸው ሰዎች ውስጥ በየቀኑ ከአንድ ሺህ በላይ የሚሆኑት በቫይረሱ እንደሚያዙ ጠቅሰዋል፡፡ በጽኑ ሕክምና ክፍል ገብተው የሚሰቃዩና ህይወታቸውን እያጡ ያሉ ሰዎች ቁጥርም ከፍተኛ ደረጃ ላይ መደረሱን አመላክተዋል፡፡
በሽታውን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ለመከላከል እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ እያደረሰ ካለው ጉዳት አኳያ ኅብረተሰቡ እያደረገ ያለው ጥንቃቄ አናሳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
“ሁላችንም የሚቆጣጠረንን አካል ሳንጠብቅና ሳንሰለች ለመመሪያውና ለመከላከያ መንገዶች ተግባራዊነት ሁሌም ቢሆን ተቀናጅተን ልንሠራ ይገባል” ብለዋል ዶክተር ሊያ፡፡
የኮሮናቫይረስ ክትባት የሚወስዱ ዜጎች በንቃት በመሳተፍ ክትባቱን እንዲወስዱ ጥሪ አቅርበዋል። “ክትባቱ የቫይረሱን የመከላከያ መንገዶችን የሚተካ ባለመሆኑ ለአፍታም ቢሆን ያለመዘናጋት ጥንቃቄዎችን መተግበር ያስፈልጋል” ነው ያሉት፡፡
በእምነት ተቋማት፣ በገበያና በትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የኮሮናቫይረስ መከላከያ መንገዶችን በአግባቡ እንዲተገበር ሚኒስትሯ አሳሰበዋል።
ሚኒስትሯ ወረርሽኙን ለመከላከል እየተደረገ ባለው ጥረት የጤና አገልግሎት በመስጠት ላይ ላሉ የጤና ባለሙያዎችና ሠራተኞች ምስጋና ማቅረባቸውን ከጤና ሚኒስቴር የማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ