
በአጣዬ ከተማ በነበረው የጸጥታ ችግር የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ ጥሪ ቀረበ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 22/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በአጣዬ ከተማ በነበረው የጸጥታ ችግር አካባቢው ወደ ሰላምና መረጋጋት በመመለሱ የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ የኢፌዴሪ መከላከያ ጥሪ አስተላለፈ።
የኢፌዴሪ መከላከያ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ እንደገለጹት በአጣዬ ከተማ ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር ወደ ሰላምና መረጋጋት ተመልሷል። የሀገር መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ አካላት በትብብር ባከናወኑት የፀጥታ ማስከበር ሥራ በአሁኑ ወቅት አካባቢው ወደ ሰላምና መረጋጋት መምጣቱን ተናግረዋል።
በመሆኑም በነበረው የጸጥታ ችግር የተፈናቀሉ ወገኖች ወደየቀዬአቸው እንዲመለሱ ጥሪ አስተላልፈዋል። ወደ ቀዬአቸው ለሚመለሱ ሁሉ ሠራዊቱ አስፈላጊውን ጥበቃና ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።
በአሁኑ ወቅት በርካቶች ወደ ቀዬአቸው እየተመለሱ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት በመፈጠሩ ቀሪዎችም እንዲመለሱ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በጸጥታ ችግሩ ለተጎዱ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ እየተደረገ ሲሆን ተቋርጦ የነበረው የትራንስፖርት አገልግሎትም መጀመሩን ገልጸዋል። በአካባቢው የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ሕዝቡን በማወያያት እያረጋጋ እና ሰላም የማስከበር ሥራ በማከናወን ላይ መሆኑን ኮሎኔል ጌትነት ተናግረዋል።
አጣዬ ከተማ ወደ ሰላምና መረጋጋት ብትመለስም አሁንም በዜጎች ላይ የስነ ልቦና ጫናና ስጋት ለመፍጠር የሚነዙ መሰረተ ቢስ አሉባልታዎች መኖራቸውን ገልጸዋል። “የጠላት ኃይሎች ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ፍላጎት ቢኖራቸውም አይሳካላቸውም” ብለዋል።
በአጣዬ ከተማ በሰውና በንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት አሳዛኝ እንደሆነ ገልጸው፤ የደረሰው ጉዳት ተጣርቶ ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ ጠቁመዋል። ዘገባው የኢዜአ ነው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ