የቆዳና ሌጦ ጥራትን ለማስጠበቅ እርድን በሰለጠኑ ባለሙያዎች በቄራ ማከናወን እንደሚገባ የአማራ ክልል እንስሳት ሀብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ አሳሰበ፡፡

300
የቆዳና ሌጦ ጥራትን ለማስጠበቅ እርድን በሰለጠኑ ባለሙያዎች በቄራ ማከናወን እንደሚገባ የአማራ ክልል እንስሳት ሀብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ አሳሰበ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 22/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በዓል በመጣ ጊዜ በብዛት የእንሰሳት እርድ ይፈጸማል፡፡ ይሁን እንጅ ቆዳ እና ሌጦ ለሀገር የሚያስገኘውን የውጭ ምንዛሬ የሚያስበው ሰው ከዚህ ግባ የሚባልም አይደለም፡፡ ጌጤ ምስጋናው ይባላሉ የባሕርዳር ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ በበዓልም ይሁን በአዘቦት ጊዜ እርድ ሲፈጽሙ ለስጋ እንጅ ለቆዳ ጥንቃቄ ስለማያደርጉ ብዙ ጊዜ የቆዳ ብልሽት እንደሚያጋጥማቸው ነግረውናል፡፡
መንግሥት በከተሞች የሚገኙትን ቄራዎች እና የእርድ ቦታዎችን ደረጃ በማሻሻል በሰለጠነ ባለሙያ እርድ እንዲፈጸም ማድርግ እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ የበግ እና የፍየል ቄራም ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡
አቶ አንባቸው ወርቅነሕ ደግሞ በባሕረ ዳር ከተማ ቆዳን ከግለሰብ በመረከብ ለማዕከላዊ ገበያ ያቀርባሉ፡፡ ይሁን እንጅ በበዓላት ወቅት እርድ ሙያው በሌላቸው ሰዎች ስለሚከናወን የቆዳ ብክነት እየተፈጠረ መኾኑን ነግረውናል፡፡ አቶ አንባቸው እንዳሉት የቆዳና ሌጦ ብክነትን ለመቀነስ እርዱ ሙያው ባላቸው ሰዎች በቄራዎች መፈጸም አለበት፡፡ ከታረደ በኋላም እስከ አራት ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ከነጋዴዎች መድረስ እንዳለበት መክረዋል፡፡
የአማራ ክልል እንስሳት ሀብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ የእንስሳት ምርት እና ተዋጽኦ ባለሙያ ደመላሽ አይችሌ እንዳሉት በ2013 በጀት ዓመት በክልሉ 7 ነጥብ 6 ሚሊዮን ቆዳና ሌጦ ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ ነበር፡፡ በዘጠኝ ወሩ 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ቆዳና ሌጦ ለማቅረብ ታቅዶ 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ቆዳና ሌጦ ለማዕከላዊ ገበያ ቀርቧል፡፡
ከዓመቱ 63 በመቶ ከዘጠኝ ወሩ ደግሞ 105 በመቶ ማሳካት ተችሏል ብለዋል፡፡ ለማእከላዊ ገበያ ከቀረበው ቆዳና ሌጦ ውሥጥ 52 በመቶ የሚሆነው የበግ ሌጦ ነው፡፡ በዘጠኝ ወሩ ለማዕከላዊ ገበያ ከቀረበው ቆዳና ሌጦም 228 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል፡፡
አቶ ደመላሽ አይችሌ እንደነገሩ በክልሉ ፈቃድ አውጥተው የሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎች ከማኅበረሰቡ በመሰብሰብ ነው ለማዕከላዊ ገበያ እና በክልሉ ለሚገኙ የቆዳና ሌጦ ፋብሪካዎች እያቀረቡ የሚገኙት፡፡ በዘጠኝ ወሩ ይህን ያህል ቆዳና ሌጦ ለማእከላዊ ገበያ ቢቀርብም በከተሞች በተዘጋጁ ቄራዎች እና በሰለጠኑ ባለሙያዎች በመታገዝ እርድ ስለማይከናዎን በቆዳው ላይ የጥራት ችግር እያስከተለ መሆኑን ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡
ጥራት ያለው ቆዳና ሌጦ ለገበያ እንዲቀርብ የሚመለከታቸው ተቋማት ቅንጅታዊ ሥራም ዝቅተኛ መሆኑን አንስተዋል፡፡ የቆዳና ሌጦ ጥራትን ለማስጠበቅ በእርድ ወቅት ብቻ ሳይሆን ከእርድ በፊት እና ከእርድ በኋላም ጥንቃቄ ማድርግ እንደሚገባ ባለሙያው አስገንዝበዋል፡፡
በዚህም የእንስሳትን የመኖ አጠቃቀም ማስተካከል፣ ቆዳን የሚጎዱ የውጭ ጥገኛ ተዋሕሲያንን ክትትል ማድርግ፣ የእንስሳት እንክብካቤ እና አያያዝን ማሻሻል ይገባልም ብለዋል ባለሙያው፡፡ በቀጣይ ጥራቱን የጠበቀ ቆዳና ሌጦ ለማግኘት ከተፈለገ በክልሉ በሚገኙ ከተሞች ዘመናዊ የእርድ ቄራዎችን ማቋቋም እንደሚገባ መክረዋል፡፡ እርዱም በሰለጠኑ ባለሙያዎች መከናወን አለበት ብለዋል፡፡ ማኅበረሰቡ ለዕርድ በተዘጋጁ ቄራዎች እና ማረጃ ቦታዎች እርድ እንዲፈጽምም አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“እነሆ ሁሉም ነገር ተፈጸመ”
Next articleበአጣዬ ከተማ በነበረው የጸጥታ ችግር የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ ጥሪ ቀረበ፡፡