“አሁን በዓልን ከልጄ ጋር ተደስቼ እውላለሁ…” ወይዘሮ አንጓች ተባባል

111
“አሁን በዓልን ከልጄ ጋር ተደስቼ እውላለሁ…” ወይዘሮ አንጓች ተባባል
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 21/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ አዲስዓለም ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ ሕይወታቸው በሥራ አጥነት፣ በኑሮ ውድነት እና ከአቅማቸው በላይ በሆነ የቤት ኪራይ ክፍያ ተጎሳቁሎ በድህነት ዘመናትን እያሳለፉ ነው፡፡ ልጃቸው የአዕምሮ ሕመምተኛ መሆኗ ደግሞ ችግራቸውን አባብሶታል፡፡ በአንድ በኩል የእለት ጉርሳቸውን ለማሟላት፤ በሌላ በኩል ደግሞ በሕመምተኛ ልጃቸው ላይ ክፉ ነገር እንዳይደርስ በአቅማቸው ልክ ጥረዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ ከዕለት ወደ ዕለት ሕይወት እየከበዳቸው ነው፤ እናም የበዓል ቀናቸውን ሳይቀር በትካዜ እንዲያሳልፉ ተገድደዋል፡፡ “ልጄ ከጎረቤት እያዬች ትሳሳለች እንጂ እኔስ አንዴ ለምጀዋለሁ” በማለት ከችግራቸው በላይ ስለልጃቸው አብዝተው እንደሚጨነቁ ነግረውናል፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ችግራቸውን በጊዜያዊነት አስታግሶ የበዓል ቀናቸውን በደስታ እንዲያሳልፉ ምክንያት አግኝተዋል፡፡
የጥላ በጎ አድራጎት ፈቃድ ማኅበር የትንሳዔ በዓልን ምክንያት በማድረግ በራሳቸው ወጪ በዓል ማክበር ለማይችሉ ወገኖች ስጦታ አበርክቷል፡፡ “ለሰው እንኑር ያለንን እናካፍል!” የሚል መርህ ያለው ማኅበሩ የተመሠረተው በተማሪዎች ሲሆን 51 አባላት አሉት፡፡ ከተመሠረተ ጀምሮ አቅም ለሌላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ልዩ ልዩ ድጋፍ አድርጓል፡፡ በሃይማኖታዊ በዓላትና በተለያዩ ማኅበራዊ ሁነቶችም በበጎ አድራጎት እየተሳተፈ ይገኛል፡፡
የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ሸጋው አስራት እንዳሉት አምስት ችግረኞችን በቋሚነት በመደገፍ ሥራውን የጀምረው ማኅበሩ አሁን በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ኾኖም በቋሚነት የሚደግፋቸው ሰዎች ቁጥር 20 ደርሷል፡፡ ወደፊትም አቅሙን እያሳደገ የሚረዳቸውን ሰዎች ቁጥር ለመጨመር አቅዷል፡፡ ለመጪው የትንሣኤ በዓል ችግረኞችን ለመርዳት በባሕር ዳር ከተማ ከዲያስፖራ፣ ከአየር ጤና፣ ከአዲስ ዓለም፣ ከዓባይራስ እና ከጠይማ ቀበሌ ነዋሪዎች 16 ሺህ 635 ብር ሰብስቧል፡፡ በዚህም ዛሬ ለ20 ሰዎች አንድ ዶሮ፣ አንድ ሊትር ዘይት እና ሁለት ኪሎ ሽንኩርት በማበርከት ችግረኞች በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ ምክንያት ሆኗል፡፡
ወይዘሮ አንጓች “አሁን በዓልን ከልጄ ጋር ተደስቼ እውላለሁ፤ ከፍ ያለ ማዕረግና እንጀራ ይስጥልኝ” ብለዋል፡፡ ወጣቶችንም መርቀዋል፣ ሌሎች ድጋፍ የተደረገላቸው ወገኖችም በተደረገላቸው ድጋፍ ተደስተዋል፤ ምስጋናም አቅርበዋል፡፡
የአዲስ ዓለም ቀበሌ የሥራ አስፈጻሚዎች ተገኝተው ድጋፉን ለተቸገሩ ሰዎች አስረክበዋል፡፡ ለተቀደሰ ዓላማ የተደራጁት ወጣቶች ቤት ለቤት ተዘዋውረው ባገኙት ሀብት ያደረጉትን ድጋፍም አድንቀዋል፡፡ መንግሥት ወጣቶቹ እንዲጠናከሩ የበኩሉን ይወጣል በማለትም ሌሎች ወጣቶችም ይህንን አርዓያ ቢከተሉ መልካም እንደሆነ መክረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleሀገራቸውን በዓለም አደባባይ ከፍ ያደረጉ የኢትዮጵያውያን ባለዉለታው፣ የኮሪያው ዘማች አርበኛ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡
Next article“እነሆ ሁሉም ነገር ተፈጸመ”