
በበዓል ወቅት በሚጣል ቆሻሻ ለበሽታ ከመጋለጥ ሁሉም ዜጋ አካባቢውን በአግባቡ በማጽዳት ኀላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ የዳንግላ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 21/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የደረቅ እና ፈሳሽ ቆሻሻን በአግባቡ አለማስወገድ ለጤና ጠንቅ ከመሆኑም በላይ የአካባቢ ንጽህናን ይጎዳል፡፡ ይህ ችግር ደግሞ በከተሞች አካባቢ በስፋት ይስተዋላል፡፡ በተለይም በበዓል ሰሞን በየቦታው የሚጣሉ የዕርድ ተረፈ ምርቶች በነዋሪዎች ላይ የጤና ችግር፣ አካባቢን ደግሞ ለብክለት ይዳርጋሉ፡፡ በመሆኑም ከወዲሁ ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ዳንግላ ከተማ አስተዳደር የደረቅና የፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድን ተዘዋውሮ ተመልክቷል፡፡ የከተማዋን ዋና አስፋልት መንገድ ጨምሮ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ላይ ደረቅ ቆሻሻ ተጥሎ ይስተዋላል፤ የውኃ ማፋሰሻ ቦዮች በደረቅ ቆሻሻ ተሞልተዋል፤ በየሰፈሩ ከየቤቱ የወጣ ያልተወገደ እና የተጠራቀመ የቆሻሻ ሽታ ለነዋሪው ብቻ ሳይሆን ለአላፊ አግዳሚው ይረብሻል፤ የበዓል ተረፈ ምርት ሲጨመርበት ደግሞ የሚፈጥረው መጥፎ ሽታ አሳሳቢ ነው፡፡
የዳንግላ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ብርቱካን እጅጉም የዚህ ሀሳብ ተጋሪ ናቸው፡፡ በመንግሥት በተመቻቸላቸው ቦታ ሻይ እና ቡና በመሸጥ የሚተዳደሩት ወይዘሮ ብርቱካን እንዳሉት በሥራ ቦታቸው አቅራቢያ ነዋሪዎች በየቀኑ ደረቅ ቆሻሻ ስለሚጥሉ በሥራቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሮባቸዋል፡፡ ይህም ለሥራቸው እንቅፋት፣ ለጤናቸው ደግሞ እክል መፍጠሩን ነግረውናል። ችግሩን ለመፍታትም ከተማ አሥተዳደሩ ደረጃውን የጠበቀ የደረቅ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ ማዘጋጀት እንዳለበት እና ነዋሪዎች ደግሞ በጊዜአዊነትም ቢሆን ቆሻሻን በየቦታው ከመጣል ይልቅ ጉድጓድ በመቆፈር መቅበር ይኖርባቸዋል ብለዋል።
አቶ ሰማኽኝ አለኽኝ ሌላው የዳንግላ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ የዳንግላ ከተማ ጥንታዊ እና የቱሪስት መዳረሻ ብትሆንም ከታሪኳ እና ከእድገቷ ጋር የሚመጥን የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ “ማኅበረሰቡ ቆሻሻን በአግባቡ የማስወገድ ልምድ የለውም” ሲሉም ድርጊቱ መስተካከል እንዳለበት መክረዋል፡፡
አንዳንድ ነዋሪዎችም በተለይ የበዓል ወቅት የዕርድ ተረፈ ምርትን ጨለማን ተገን አድርገው በየቦታው እንደሚጥሉ ነግረውናል። “እንዲህ ዓይነት ኋላ ቀር ልምድ ብዙዎች አፍንጫቸውን በእጃቸው ሸፍነው እንዲጓዙ እና ለተጓዳኝ በሽታ እንዲጋለጡ እያደረጋቸው ነው” ብለዋል፡፡ እሳቸው ምን ያህል ኀላፊነታቸውን እየተወጡ እንደሆነ ላቀረብንላቸው ጥያቄም ጋሪ ተከራይተው ቆሻሻን በጊዜያዊነት በተቆፈረ ጉድጓድ እንደሚያስወግዱ ተናግረዋል።
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ሠላም አየነ እንደገለጹት ደረቅ ቆሻሻ በየቦታው መጣል የከተማዋን ገጽታ ስለሚያበላሽ ከተማ አሥተዳደሩ የአወጋገድ ሥርዓቱን ማዘመን አለበት። በበዓል ወቅት በሚጣል ቆሻሻ ለበሽታ ከመጋለጥ ሁሉም ዜጋ በባለቤትነት ለከተማዋ ንጽህና መጨነቅ እንዳለበትና ከተማ አሥተዳደሩም በጽዳት የተሰማሩ ወጣቶችን ማበረታታት ይገባዋል ብለዋል።
የዳንግላ ከተማ አስተዳደር ከተማ ልማትና ቤቶች ኮንስትራክሽን ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስያኪጅ ግዛቸው አጠና እንደገለጹት በበዓል ወቅት የዕርድ ተረፈ ምርቶችን በአግባቡ ማስወገድ እንዳለበት ከነዋሪው ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ ሁሉም ሰው ከሚኖርበት ቤት እስከ 50 ሜትር ያለውን አካባቢ እንዲያጸዳ መግባባታቸውንም ገልጸዋል፡፡ በተደረገው ውይይት መሠረት አብዛኛው ማኅበረሰብ ቢያጸዳም ውጤታማ ግን አይደለም ብለዋል። በቀጣይ ከትልልቅ ከተሞች ልምድ በመውሰድ ደረቅ እና ፈሳሽ ቆሻሻን የሚያስወግዱ ማኅበራትን የማበረታታት እና የመደገፍ ሥራ ይሠራል ብለዋል፡፡
በደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ላይ የተጀመሩ ሥራዎች እንደነበሩ የጠቀሱት ሥራ አስኪያጁ በወቅቱ ገንዘብ ካለመክፈል ጋር ተያይዞ ቅሬታ በመፈጠሩ ጉዳዩ ለምክር ቤት ቀርቦ ውይይት እንደተደረገበት እና ነዋሪው ለሚያስወግደው ቆሻሻ ተመጣጣኝ ገንዘብ መክፈል እንዳለበት መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡
የተዘጉ የውኃ ማፋሰሻ ቦዮችን የማስከፈት ሥራም እየተከናወነ እንደሚገኝ ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል። በከተማ አሥተዳደሩ ቋሚ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ቦታ ለመገንባት በሂደት ላይ መሆኑንም አቶ ግዛቸው አስታውቀዋል፡፡ የከተማዋ ነዋሪዎችም ከተማ አሥተዳደሩ ባዘጋጀው ጊዜያዊ የደረቅ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ መጠቀም እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ:- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ