በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በቻግኒ ራንች ለሚገኙ ተፈናቃዮች የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ፡፡

144
በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በቻግኒ ራንች ለሚገኙ ተፈናቃዮች የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 21/2013 ዓ.ም (አሚኮ) መኖሪያቸውን በሰሜን አሜሪካ ያደረጉት ኢትዮጵያውያን ከሀገራቸው ርቀው ቢኖሩም የሀገራቸው መቸገር የእነሱም መቸገር መሆኑን በመገንዘብ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው ለሚገኙ ዜጎች ማቋቋሚያ የሚውል 14 ሚሊየን ብር የሚገመት የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ የድጋፉ አስተባባሪዎች ያሰባሰቡትን የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ በቻግኒ ራንች በመገኘት አስረክበዋል፡፡
ድጋፉን ያስረከቡት በሰሜን አሜሪካ በደብረ መንክራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል ኀላፊ መላከኃይል ቀሲስ እስክንድር እንዳሉት በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና አቢያተ ክርስቲያናት በመመካከር በአምስት ቀን ውስጥ ድጋፉን በማሰባሰብ ነው የለገሱት፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሰብሳቢነት ድጋፉ ይሰብሰብ እንጅ የተለያዩ እምነት ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎችም በድጋፉ እንደተሳተፉ ተናግረዋል፡፡
የምግብ እህልና ሌሎች የቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን የተናገሩት መላከኃይል ቀሲስ እስክንድር ሁሉም ከተባበረ በኢትዮጵያ የሚታየውን ችግር ማስወገድ ይቻላል ብለዋል፡፡
በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከተፈናቀሉት ጎን በመቆም መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት እገዛ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡
በቀጣይም በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና አቢያተ ክርስቲያናት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው ያረጋገጡት፡፡
በቻግኒ ራንች የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ አስተባበሪ ጌቴ ምህረቴ እንደገለጹት ከበጎ አድራጊዎች የሚለገሱትን ድጋፎች በፍትሐዊነት ለተፈናቃዮቹ ይከፋፈላሉ፡፡ ከሀገር ውጭም ይሁን በሀገር ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የተፈናቀሉትን መልሶ ማቋቋም ላይ ሊረባረቡ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ አቶ ጌቴ በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ያሳዩት ወገንተኝነት ለሌሎችም አረአያ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ብርቱካን ታየ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleመንግሥት ከስድስት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በትግራይ ክልል ለተፈናቃዮች እና ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች የሚሰጠው ሁሉአቀፍ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለጸ፡፡
Next articleበበዓል ወቅት በሚጣል ቆሻሻ ለበሽታ ከመጋለጥ ሁሉም ዜጋ አካባቢውን በአግባቡ በማጽዳት ኀላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ የዳንግላ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡