
በአጣዬና በጭልጋ አካባቢዎች በወንጀል ድርጊት የተሳተፉ አካላትን በአጭር ጊዜ ለሕግ ለማቅረብ ሕዝቡ ትብብር እንዲያደርግ
ተጠየቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 20/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በአጣዬና አካባቢው እንዲሁም በጭልጋ አካባቢ የተፈጠረውን የወንጀል ድርጊት
ለማጣራት የተቋቋመው መርማሪ ቡድን ውጤታማ እንዲሆን ሕዝቡ ተገቢውን ትብብር እንዲያደርግ የአማራ ክልል ጠቅላይ
ዐቃቤ ሕግ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በአጣዬና በማዕከላዊ ጎንደር ጭልጋ አካባቢ የተፈጸመውን የወንጀል ድርጊት የሚያጣራ የምርመራ ቡድን ተቋቁሞ ወደ ስፍራው
መላኩን የአማራ ክልል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አስታውቋል፡፡ የጠቅላይ አቃቤ ሕግ መስሪያ ቤት ሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አለምሸት
ምሕረቴ እንዳሉት የምርመራ ቡድኑ ከፌዴራልና ከክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እንዲሁም ከፖሊስ የተውጣጡ አባላት የተካተቱበት
ነው፡፡ ቡድኑ ሲቋቋም ዝርዝር ውይይት ተደርጓልም ብለዋል፡፡
በአጣዬና አካባቢው በተፈጸመው የተደራጀ የወንጀል ድርጊት የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ የአካል መጉደል ደርሷል፤ ንብረት ወድሟል፤
በርካታ ሰዎች መፈናቀላቸውንም አሚኮ በተደጋጋሚ የዘገባ ሽፋን ሰጥቷል፡፡ የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግም ድርጊቱ ተራ ግጭት
አለመኾኑን ጠቅሷል፡፡ ይህንን ድርጊት ለማጣራትም የምርመራ ቡድኑ ዕቅድ በማዘጋጀት ሥራ መጀመሩን ነው የሕዝብ ግንኙነት
ኀላፊው ያስታወቁት፡፡
በዕቅዱ መሠረት በወንጀል ድርጊቱ የተሳተፉ አካላትን በአጭር ጊዜ ወደ ሕግ የማቅረብ ሥራ ይከናወናል፤ የምርመራ ሂደቱ
ውጤታማ እንዲኾን ማኅበረሰቡ ትክክለኛና ተገቢውን ትብብር እንዲያደርግም ጥሪ ቀርቧል፡፡ ትክክለኛ መረጃ መስጠት፣ ማስረጃ
ማቅረብና ምስክር መኾን ከማኅበረሰቡ ይጠበቃል፡፡ በምርመራ ሂደቱ የሚገኝ መረጃ ለሕዝብ ይፋ ይደረጋልም ብለዋል የሕዝብ
ግንኙት ኀላፊው፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m