
“የላልይበላ ብሔራዊ የንብ ሃብት ሙዚየም ዛሬም በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ አልገባም”
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 20/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የላልይበላ ብሔራዊ የንብ ሃብት ሙዚየም በ2000 ዓ.ም ነበር የመሰረተ ድንጋዩ
የተቀመጠው፤ በ2003 ዓ.ም ደግሞ ግንባታው ተጀምሯል፡፡ በአንድ መቶ ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ሙዚየሙ ከ300 ሚሊዮን
ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል፡፡ ሙዚየሙ የአካባቢውን አርሶ አደሮች ማሰልጠን፣ የተሻሻሉ አሠራሮችን ማሳየት፣ ማር በማጣራት
ለሀገር ውስጥ፣ ወደ ውጭ ለመላክ እና የቴክኖሎጅ ሽግግር ለማድረግ ዓላማው አድርጎ ነበር የተገነባው፡፡
የሙዚየሙ ሥራ አስኪያጁ ሲሳይ ደጀኔ እንዳሉት የላስታ አካባቢ አግሮ ኢኮሎጅ ለንብ ማነብ የተመቼ መሆኑም ለሙዚየሙ
መገንባት ሌላኛው ምክንያት ነው፡፡ ሥራ አስኪያጁ እንዳሉት ሙዚየሙን በአምስት ዓመት ውስጥ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ
ለማስገባት ታሳቢ በማድረግ ከ2011 ዓ.ም መጀመሪያ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር
ደግሞ 80 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ታሳቢ ተደርጎ ነበር ወደ ሥራ የተገባው፡፡
በዚህ ወቅት በሁለት የንብ እርባታ ጣቢያዎች ከ100 በላይ የንብ መንጋ መኖራቸውን ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡ ከተለያዩ
ድርጅቶች ጋር በመተባበር በንብ እርባታ ዙሪያ ሥልጠናም ተጀምሯል፡፡ የቀሰም እጽዋት የማልማት ሥራ መሠራቱንም
ነግረውናል፡፡ አዳራሾችን እና መዝናኛ ክበቦችን የኅብት ምንጭ ለማድርግ የገቢ አሰባሰብ እና አጠቃቀም መመሪያ ተዘጋጅቷል፡፡
የጥናት እና ምርምር ሥራ ለመሥራት የሚያስችሉ የቤተ ሙከራ ዕቃዎችን የማሟላት ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡
ይሁን እንጅ እቃዎች ከፍተኛ ገንዘብ ስለሚጠይቁ እና ክልሉ ካለው በጀት እጥረት አሁንም ሙሉ በሙሉ አሟልቶ ሥራ
ለማስጀመር አለመቻሉን አንስተዋል፡፡ ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡
በክልሉ ከሚገኙ 10 ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጋራ ለመሥራት ስምምነት ላይ መደረሱንም ነግረውናል፡፡ ሙዚየሙ በሀገሪቱ የጥናት
እና የምርምር ማዕከል ሆኖ እንዲያገለግል ደግሞ ከምሁራን ጋር ምክክር ተደርጓል፡፡ በዚህም መንግሥት እሴት ጨምሮ ማር
ከመሸጥ ወጥቶ አርሶ አደሮች በንብ ማነብ እንዲሰማሩ፣ ባለሃብቶች ደግሞ እሴት ጨምረው ማምረት እንዲችሉ የሚያስችል
ማሰልጠኛ እና የምርምር ማዕከል እንዲሆን ለማድረግ ውይይት ተደርጓል፡፡
አደረጃጀቱ ተመራማሪዎችን እና ምሁራንን እንዲያካትት እና የሙዚየሙ “ጋለሪ” የሰው ኃይል አደረጃጀት መስተካከል እንዳለበት
በመታመኑ ምሁራን እንደገና እንዲያጠኑ መደረጉንም ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡ ሙዚየሙ ለምን ላልይበላ ላይ እንዲቋቋም
ተደረገ? ተብሎ ለተነሳው ጥያቄ ሲመልሱም አካባቢውን በዓመት እስከ 100 ሺህ ጎብኝዎች የሚጎበኙት በመሆኑ የሀገሪቱን
የማር ምርት ለዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ በቀላሉ የማስተዋወቅ እድሉ ሰፊ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡
ላልይበላ የሚለው የቅዱስ ላልይበላ ስያሜ ‹ማር ይበላ› የሚል ትርጉም ስላለው የማር ምርቱን በላልይበላ ሥም ለመወከል
ታሳቢ የተደረገ መሆኑንም ነግረውናል፡፡ ከዚህም ባሻገር ጎብኝዎች ከውቅር አብያተ ክርስቲያናቱ በተጨማሪ ሙዚየሙንም
እንዲጎበኙ በማድረግ የጎብኝዎችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም ታሳቢ ተደርጓል፡፡ ሙዚየሙ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ ለ74 ዜጎች
የሥራ እድል ይፈጥራል፡፡ በዚህ ወቅት በሙዚየሙ 20 የሰው ኃይል ቅጥር ተፈጽሞ በሥራ ላይ ይገኛሉ፡፡
ሙዚየሙ የተቋቋመው ከላስታ አካባቢ በተጨማሪ የሰሜን እና የደቡብ ጎንደር፣ የሰሜን ወሎ፣ የዋግን እና የትግራይን
አካባቢዎች የማር ምርት አቅም ታሳቢ ተደርጎ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ አንስተዋል፡፡
ሙዚየሙ ከንብ ማነብ በተጨማሪ ቤተመጽሐፍት፣ ማሰልጠኛና የምርምር ማዕከል፣ የተለያዩ የስብሰባ አዳራሾች፣ ቢሮዎች፣
ባሕላዊ መመገቢያ፣ የንብ አናቢዎች መኖሪያ ቤትና ሌሎችንም ማካተቱን ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m