
“የኮሮናቫይረስ ክትባት የጤና ችግር እንደሚያስከትል ተደርጎ የሚነሳው ሀሳብ ትክክል አደለም” የክትባቱ ተጠቃሚ
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 20/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የኮሮናቫይረስ ክትባት መሰጠት ከተጀመረ አንድ ወር አስቆጥሯል፡፡ ይሁን እንጅ ክትባቱን አስመልክቶ በማኅበረሰቡ ዘንድ
የተለያዩ አመለካከቶች ተስተውለዋል፡፡
አቶ እንዳወቀ ገላው ክትባቱን ከወሰዱ ሰዎች ውስጥ እንዱ ናቸው፡፡ አቶ እንዳወቀ እንዳሉት ማኅበረሰቡ በክትባቱ ላይ የተለያየ አመለካከት ቢኖረውም የሚነዛውን አሉባልታ
ወደጎን በመተው ክትባቱን እንደወሰዱ ተናግረዋል፡፡ ከተከተቡ በኋላም በጤናቸው ላይ ያመጣው ችግር አለመኖሩን ገልጸውልናል፡፡ ክትባቱ የጤና ችግር እንደሚያስከትል
ተደርጎ የሚነሳው ሀሳብም ትክክል አለመሆኑን ተናግረዋል።
ማኅበረሰቡም በዚህ ወቅት የኮሮናቫይረስ ስርጭት እየጨመረ እና ሕይወት እየቀጠፈ መኾኑን ተረድቶ እንዲከተብ መክረዋል፡፡ የጤና ተቋማትም ከሌሎች መሥሪያ ቤቶች
ጋር በመቀናጀት ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ መፍጠር እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የሽንብጥ ጤና ጣቢያ ኀላፊ ራሄል ፍራንኮ እንዳሉት ስለ ክትባቱ አጠቃላይ ሁኔታ ለማኅበረሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እየተሰጠ
ይገኛል፡፡ በዚህም በመጀመሪያዎቹ የክትባቱ መስጫ ወቅት ሥለ ክትባቱ የነበረው የተዛባ አመለካከት በመስተካከሉ የማኅበረሰቡ የመከተብ ፍላጎት እየጨመረ እንደሚገኝ
ነግረውናል፡፡
አሁን ላይ እድሜያቸው 55 ዓመት እና ከዚያ በላይ ተጓዳኝ የጤና ችግር ያለባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁም ከ65 ዓመት በላይ ደግሞ ዕድሜን መሰረት ያደረገ
ክትባት እየተሰጠ ቢሆንም ከ55 ዓመት በታች ተጓዳኝ የጤና ችግር ያለባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ለመከተብ ጥያቄ እያቀረቡ እንደሚገኙ ኀላፊዋ አንስተዋል፡፡
በቀጣይ መንግሥት እነዚህን እና ሌሎች ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭ የኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ የክትባት ፕሮግራም አስተባባሪ ወርቅነህ ማሞ የኮሮናቫይረስ ክትባት በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ መሰጠት ከጀመረ አንድ ወር ማስቆጠሩን
አንስተዋል፡፡ ይሁን እንጅ ክትባቱ ‹‹ተጓዳኝ ችግር ያመጣል ›› በሚል በማኅበረሰቡ መጠራጠሮች ተስተውለዋል፡፡ ክትባቶች እና መድኃኒቶች ሥራ ላይ የሚውሉት ጥራታቸው
እና የሚያስፈልገው መስፈርት ማሟላታቸው በዓለም ጤና ድርጅት ሲረጋገጥ መኾኑን አቶ ወርቅነህ አንስተዋል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅትም ስለክትባቱ የሚለቀቁ መረጃዎች ሀሰት መኾናቸውን እና ከክትባቱ ጋር ተያያዥነት የሌላቸው መኾናቸውን መግለጫ በማውጣቱ ሀገሮች እየተከተቡ
እንደሚገኙ አስተባባሪው ጠቅሰዋል፡፡
በኢትዮጵያም የህሙማን እና የሞት ቁጥሩ እየጨመረ በመኾኑ ማኅበረሰቡ ክትባቱን መውስድ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ማኀበረሰቡ መረጃዎችን ትክክለኛነት ከዓለም ጤና ድርጅት እና መንግሥት ከሚያወጣቸው መረጃዎች ማረጋገጥ እንደሚገባው ነው የጠቆሙት፡፡
አሁን ላይ ክትባቱ በሁሉም የመንግሥት ጤና ተቋማት እየተሰጠ እንደሆነ አንስተዋል፡፡ እስከ ሚያዝያ 19/2013 ዓ.ም ከ56 ሺህ 300 በላይ የጤና ተቋማት ሠራተኞች፣
እድሜያቸው ከ55 እስከ 64 የሆኑና ተጓዳኝ የጤና ችግር ያለባቸው፣ እድሜያቸው ከ65 በላይ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ክትባቱን ወስደዋል፡፡
በዚህ ዓመት በሀገሪቱ 20 በመቶ የሚኾነው የኅብረተሰብ ክፍል ይከተባል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ከዚህ ውስጥ 3 በመቶ የሚኾነውን የኅብረተሰብ ክፍል በመጀመሪያው ዙር
ለመከተብ ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጅ በመረጃ እጥረት እና ‹‹ክትባቱ ተጓዳኝ ችግር ያመጣል›› በሚል የግንዛቤ ችግር ማኀበረሰቡ በተቀመጠው ጊዜ ባለመከተቡ
እስከ አሁን ክትባቱ እየተሰጠ መኾኑን አንስተዋል፡፡
በየትኛውም የእድሜ ክልል ውስጥ ተጓዳኝ የጤና ችግር ያለባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ቢኖሩም ካለው የክትባት መድኃኒት አቅርቦት እና የሰዎችን በሽታውን የመቋቋም
አቅም ታሳቢ በማድረግ በእድሜ ለገፉ ሰዎች ክትባቱን መስጠት ማስፈለጉን አንስተዋል፡፡
አስተባባሪው እንዳሉት በቀጣይ ለቫይረሱ ተጋላጭ ተብለው ለተለዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተዋረድ ክትባቱ ይሰጣል፤ በዚህም ሊኖር የሚችለውን መጨናነቅ ለመቀነስ
በመጀመሪያው ዙር እንዲከተቡ የተለዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ክትባቱን መውሰድ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
በሀገሪቱ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን መጠን ያለው የክትባት መድኃኒት በመጀመሪያው ዙር መግባት ችሏል፡፡ እስከ ግንቦት መጨረሻ ደግሞ 7 ነጥብ 6 ሚሊዮን መጠን ያለው
የክትባት መድኃኒት ለማስገባት ታቅዶ እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 5 ሚሊዮን መጠን ያለው የክትባት መድኃኒት ሰሞኑን መግባቱንም ነው የነገሩን፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m