ቢሮው  በአማራ ክልል ዘጠኝ “ካምፓሶች” እና ኮሌጆችን ዘጋ፡፡  

2343

ከተቀመጠላቸው መስፈርት ውጪ ሲያስተምሩ የተገኙ ዘጠኝ “ካምፓሶች” እና ኮሌጆችን ማገዱን የአማራ ክልል ቴክኒክ፣ ሙያና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ገለጸ፡፡

በክልሉ በቀንና በማታ መርሀ ግብሮች እንዲያስተምሩ እውቅና የተሰጣቸው የግል ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች 91 ብቻ ናቸው ብሏል ቢሮው፡፡ በመሆኑም ዕውቅና ከሌላቸው ኮሌጆች ተማሪዎች እንዳይመዘገቡ ነው ያሳሰበው፡፡ ከእነዚህ ውጪ በአዲስ እውቅና የተሰጠው ኮሌጅ አለመኖሩንም ነው ቢሮው ያስታወቀው፡፡

ከተቀመጠላቸው መስፈርት ውጪ ሲያስተምሩ የተገኙ ዘጠኝ “ካምፓሶች” እና ኮሌጆች መታገዳቸው የገለጸው ቢሮው ዝርዝራቸውንም ይፋ አድርጓል፡፡ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሲሰራ የነበረ ዳዲ የእርቀት ትምህርት ኮሌጅ፣ ራዳ ኮሌጅ ጎንደር ካምፓስ፣ ራዳ ኮሌጅ እንጅባራ ካምፓስ፣ ወልዲያ ከተማ የሚገኝ ኢንኮዶ ኮሌጅ፣ ደሴ ከተማ የሚገኝ ዳንዲቦር ኮሌጅ፣ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ማክሰኝት ከተማ የሚገኝ አባይ ቢዝነስና ቴክኖሎጅ ኮሌጅ፣ ሻሁራ ከተማ የሚገኝ ራስ ዳሽን ኮሌጅ፣ ደልጊ ከተማ የሚገኝ ልህቀት የቢዝነስና ቴክኖሎጅ ኮሌጅ እና ትክል ድንጋይ ከተማ የሚገኝ ጃንተከል ቢዝነስና ቴክኖሎጅ ኮሌጅ ከህግና መመሪያ ውጭ ሲያስተምሩ በመገኘታቸው እንዲዘጉ መደረጋቸውን  ነው ቢሮው የገለጸው፡፡

በነባር የትምህርት ዘርፎች ማስተማር ለሚፈልጉ አዲስ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ የግል ኮሌጆች ከዚህ በኋላ አዲስ የእውቅና ፈቃድ እንደማይሰጥም  መገለጹን ከክልሉ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

ምክንያቱ ደግሞ ከ2009 ዓ.ም እስከ 2012 ዓ.ም በተሰራ የገበያ ጥናት እስካሁን በተፈቀዱ ዘርፎች እየተማረ የሚገኘው የሰው ሀይል ከበቂ በላይ በመሆኑ እና ሰልጣኞች ተመርቀው በሚፈለገው ልክ ወደ ገበያው ባለመቀላቀላቸው ነው ተብሏል፡፡

 

 

Previous articleቺርቤዋ 30 12 2011
Next articleአስገራሚ ቆይታ ከአርቲስት ይስሐቅ ባንጃው ጋር