
የዓባይ ውኃ ፍትሐዊ አጠቃቀም ዳግማዊ የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ።
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 19/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ከዓባይ ውኃ 86 በመቶ ድርሻ ያላት ኢትዮጵያ ለዘመናት ግብጽ የሲናይ በረሃን ሃሩር
በትነት የምታስታግስበትን ያክል ውኃ እንኳን ተጠቅማ አታውቅም፡፡ የቅኝ ግዛት ዘመን አሸከሮች መላው ጥቁር አፍሪካ ለነፃነት
ሲጋደል እነርሱ ግን ከወራሪዎቻቸው ፍላጎት የመነጨ የውኃ ስምምነት ውል ይፈራረሙ ነበር፡፡ ዘመን የነገሮች ሁሉ ጌታ ነውና
የዚያ ዘመን ውል ባልከፋ፤ ችግር የሆነው መላው አፍሪካ የቅኝ ግዛት ዘመን ቀንበርን ከሰበረ ከረጅም ጊዜ በኋላም ከቅኝ ግዛት
አስተሳሰብ ያልተላቀቁ መኖራቸው እንጂ፡፡
በ1929 (እ.አ.አ) የጂኦ ፖለቲካው ቀጣና የምንጊዜም ሰንኮፍ ተካይ እንግሊዝ የዓባይ ምንጭ የሆነችው ኢትዮጵያ
ያልተካተተችበት የዓባይ ውኃ ክፍፍል ስምምነት በቅኝ ግዛት የምታስተዳድራቸውን ሀገራት ይዛ ከራሷ ጋር ተፈራረመች፡፡ በወቅቱ
የእንግሊዝ አፈራራሚ እና ተፈራራሚ ሆኖ መቅረብ ለቀጣናው ዘላቂ ሠላም ከማሰብ የመነጨ ሳይሆን በከፍተኛ ደረጃ ጥሬ እቃ
ለተራቡት ኢንዱስትሪዎቿ ከጥጥ እስከ ሰሊጥ ለማቅረብ ከመፈለግ የተደረገ ብልጣብልጥ እሳቤ ነበር፡፡
ነገር ግን ከሦስት አስርት ዓመታት በኋላ ስምምነቱን የሚሽር ሌላ ጥያቄ ከተፈራራሚዎቹ አንዷ አቀረበች፡፡ ከቅኝ ግዛት ነፃ
መውጣቷን ተከትሎ “የ1929 (እ.አ.አ) የዓባይ ውኃ ስምምነት ይቀየርልኝ” ያለችው ሱዳን ለሌላ ስምምነት ከግብጽ ጋር
ተቀመጠች፡፡ በ1959ኙ ስምምነትም የዓባይን ውኃ 66 በመቶ ለግብጽ፣ 22 በመቶ ለሱዳን እና 12 በመቶ ደግሞ ለትነት ተብሎ
ተከፋፈለ፡፡ ይህም 84 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ዓመታዊ የዓባይ ውኃ ፍሰት ውስጥ 55 ነጥብ 5 ለግብፅ፣ 18 ነጥብ 5 ለሱዳን እና
10 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ለትነት መሆኑ ነበር፡፡
ለዓባይ ወንዝ የኢትዮጵያ የውኃ ድርሻ ምን ያክል እንደሆነ እየታወቀ ከውኃ ክፍፍሉ ውስጥ ልትገባ ቀርቶ ሲፈራረሙ እንኳን
አታውቅም ነበር፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ግልፅ ነው፤ የቅኝ ግዛት ቅጥቅጥ አስተሳሰብ ለኢትዮጵያ እንደማይመች ያውቁታል፡፡
ፈርዖናውያን የቅኝ ግዛት ምርኮኞቹ ከውኃ ክፍፍል ስምምነታቸው በኋላ የአስዋንን ግድብ ሲገነቡ የውኃ ምንጫችን ከኢትዮጵያ
ስለሆነ አስዋንን እየገነባን ነውና እወቁትም አላሉም፡፡ ካለፉት አስር ዓመታት ጀምሮ ኢትዮጵያ በዓባይ ውኃ አጠቃቀም ዙሪያ
ዘመንን የሚመጥን ተራማጅ አስተሳሰብ ይዛ ብቅ አለች፡፡ በዓባይ ውኃ ዙሪያ ፍትሐዊ አጠቃቀም ሊኖር ግድ ይላል ስትልም
በተደጋጋሚ ተደመጠች፡፡
2007 ዓ.ም ላይ ደግሞ የተፋሰሱን የላይኛው እና የታችኛው ሀገራት ያካተተ “ናይል ቤዚን ኢኒሸቲቭ” ተመሰረተ፡፡ ነገር ግን ለቅኝ
ግዛት ሥሪቶቹ ሀገራት ይህ አዲስ አስተሳሰብ እየጎመዘዛቸውም ቢሆን የሚፈርሙት እና የሚቀበሉት ሀቅ ሆነ፡፡
ኢትዮጵያ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጀመሯን ተከትሎ የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ብቅ ማለት ጀመረ፡፡ ነገሮች እየቆዩ
ከረሩ፤ ግብጽ በተሳሳተ ትርክት እና በተንሸዋረረ ዲፕሎማሲ የኢትዮጵያን እጅ ለመጠምዘዝ በተደጋጋሚ ሞከረች፡፡ ዛሬ እየሆነ
የሚስተዋለው እልክ እና ፍጥጫ የጅማሮው ጡዘት እንደሆነ ሁሉም ይረዳዋል፡፡
አሁን ከፓን አፍሪኒዝም እሳቤ ፈቀቅ ያለ አቋም በታሪክ አራምዳ የማታውቀው ኢትዮጵያ ፍትሐዊ የውኃ አጠቃቀም መርሆዋ
በሁሉም አፍሪካውያን ዘንድ ተቀባይነት ተችሮታል፡፡ የዚህ ዘመን የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኞች ከኬኒያ እስከ ናይጀሪያ፣ ከኢትዮጵያ
እስከ ደቡብ አፍሪካ ድምፃቸውን ለኢትዮጵያ እያሰሙ ድጋፋቸውን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እየሰጡ መሆኑን እያስተዋልን
ነው፡፡ የዓባይ ወንዝ ፍትሐዊ የውኃ አጠቃቀም ጉዳይ የተፋሰሱ ሀገራት ብቻ ከመሆን አልፎ በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር የተሰለፉ
ሀገራትን የሚመለከት አጀንዳ ነው። ምንም እንኳን የሚደመጡት ድምጾች በኢትዮጵያ ጥረት የመጡ ሳይሆኑ ከእውነት፣ ፍትሕ እና
ከአፍሪካዊ እሳቤ ተነሳሽነት የመነጩ ቢሆኑም፡፡
ከንጊንያ ዲዩ እስከ ኢድሪስ ሳኑስ፣ ከሙሃመድ አል አሩሲ እስከ ሲሳይ ዓለምአየሁ፣ ከሳሚራ ጃፋር እስከ ማርቲን ፕላውት ዓባይን
ዳግማዊ የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መድረክ አድርገውታል፡፡ ዓለም ስለእውነት እና ስለፍትሕ ለማወቅ ከፈለገ ከእነዚህ እና መሰል
የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኞች የሚወጡ ድምፆችን ለማድጥ ፍላጎት ማሳየት ሊኖርበት ግድ ይላል፡፡
የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲም እነዚህን እና መሰል የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኞች ፈለግ ተከትሎ የኢትዮጵያን እውነት ለዓለም
ሕዝብ ሊደርስ የሚገባበት ጊዜው አሁን ነው፡፡
በታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m