“የእኔ ድምጽ መስጠት ያለውን ዋጋ ስለምረዳ ከወዲሁ ለመምረጥ ካርዴን ወስጃለው” የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ

201

“የእኔ ድምጽ መስጠት ያለውን ዋጋ ስለምረዳ ከወዲሁ ለመምረጥ ካርዴን ወስጃለው” የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 19/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች በ6ኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ለመሳተፍ
የምርጫ ካርድ በማውጣት ዝግጅት እያደረጉ ነው፡፡ የከተማ ነዋሪ ወጣት አምላኬ ተመሥገን የዜግነት ግዴታውን ለመወጣት
ወሳኝ የሆነዉን የምርጫ ካርድ ወስዶ ምርጫ የሚካሄድበትን ቀን እየተጠባበቀ እንደሚገኝ ተናግሯል፡፡
“በእኔ አለመምረጥ ምክንያት ለሀገር የሚጠቅመው የፖለቲካ ፓርቲ ሊወድቅ ስለሚችል ካርዴን አውጥቻለሁ” ብሏል ወጣት
አምላኬ፡፡ የምርጫ ካርድ ለመውሰድ ያለው ጊዜ አጭር በመሆኑ በምርጫው መሳተፍ የሚችሉ ሁሉ በወቅቱ ካርዳቸውን
እንዲይዙ መክሯል፡፡
በአምስት ዓመት አንድ ጊዜ የሚካሄደውን ምርጫ በቸልተኝነት የምርጫ ካርድ ባለማውጣት እድሉ ሊያልፍ አይገባም ያሉት
ደግሞ አቶ አለልኝ ሞኝነት ናቸው፡፡ የምርጫ ካርድን ጊዜው ሳያልፍ በማውጣት ለሀገሪቱ የሚበጀውን የፖለቲካ ፓርቲ መምረጥ
ከሕዝቡ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡
የምርጫ ካርድ ባለማውጣት የሚገኝ ትርፍ እንደሌለም ነው ነዋሪው የነገሩን፡፡ “እኔ የምመርጠው የፖለቲካ ፓርቲ ለልጆቼ፣
ለእህትና ወንድሞቼ እንዲሁም ከቤተሰብ አልፎ ለሀገር ሊጠቅም ይችላል የሚል ተስፋ አለኝ” ብለዋል፡፡
ይሄነው ጌትነት የተባሉት ሌላው የባሕር ዳር ነዋሪ ደግሞ አንዳንድ ሰዎች የምርጫ ካርድ እያወጡ እንዳልሆነ ገልጸው ይህ ግን
ስህተት ነው ብለዋል፡፡ ይጠቅመኛል ወይም ሀገር ሊያስተዳድር ይችላል ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ የምርጫ ካርድ
ማውጣታቸውንም ተናግረዋል፡፡
በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ጣና ክፍለ ከተማ የምርጫ ጣቢያ 1 ሀ የመዝገብ ሹም አቶ አብርሃም ማስረሻ ከሚያዝያ 1/2013
ዓ.ም ጀምሮ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 952 ሰዎች የምርጫ ካርድ ማውጣታቸዉን ተናግረዋል፡፡
በጣቢያቸውም 1 ሺህ 500 ሰዎች የምርጫ ካርድ ይወስዳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅሰዋል፡፡ የምርጫ ካርድ የሚያወጡ
ሰዎች፣ ካርዱን ባወጡበት ቦታ መምረጥ እንዳለባቸው፣ ለምርጫ ሲመጡም ካርዳቸዉን ይዘው እንደሚመጡና ከምርጫ ሂደቱ
ጋር የተያያዙ መረጃዎችን እየሰጡ እንደሆነ አቶ አብርሃም አስረድተዋል፡፡ ምዝገባው በኦንላይን ስለሚደገፍ አንድ ሰው ሁለት ቦታ
ወይም ከዚያ በላይ ካርድ ቢያወጣ ሊጋለጥ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleበኩር ጋዜጣ ሚያዝያ 18/2013 ዓ.ም ዕትም
Next articleየዓባይ ውኃ ፍትሐዊ አጠቃቀም ዳግማዊ የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ።