ከአጣዬ እና አካባቢው ተፈናቅለው በመሐል ሜዳ የሚገኙ ዜጎች አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲቀርብላቸው ጠየቁ፡፡

174
ከአጣዬ እና አካባቢው ተፈናቅለው በመሐል ሜዳ የሚገኙ ዜጎች አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲቀርብላቸው ጠየቁ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 17/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በርካታ ንፁሃንን ለህልፈት እና ለንብረት ውድመት የዳረገው የአጣዬ እና አካባቢው ጥቃት ያደረሰው ሰብዓዊ ኪሳራ ከባድ መሆኑን ከጥቃቱ የተረፉ ተፈናቃዮች ተናግረዋል፡፡ ከሞት ተርፈው በመሸሽ በደብረ ሲና እና በመሐል ሜዳ ከተማ አካባቢ ቁጥራቸው ከ250 ሺህ በላይ የሚደርሱ ዜጎች ተጠልለዋል፡፡ አፋጣኝ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲቀርብላቸውም አሚኮ ያነጋገራቸው በመሃል ሜዳ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ዜጎች ጠይቀዋል፡፡
ወይዘሮ ቤዛዊት ምንዳ በአጣዬ ከተማ ነዋሪ ነበሩ፡፡ ወይዘሮ ቤዛዊት እንዳሉት ባለቤታቸው በሕግ ማስከበር ዘመቻው ግዳጅ ላይ ነው፡፡ ለራሱ ሕይዎት ሳይሳሳ የሀገርን ዳር ድንበር ቀን ከሌሊት የሚያስከብረው ወታደር አምስት ቤተሰቦቹ ግን በስርዓት አልበኞች የግፍ ጭፍጨፋ እና ዘረፋ ደርሶባቸው በመሐል ሜዳ ከተማ በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ሕይዎትን ሊያሳልፉ ግድ ብሏቸዋል፡፡
ከከፍተኛ ሞቃታማ ቦታዋ አጣዬ ወደ ቀዝቃዛማዋ መሐል ሜዳ ያውም ከሞቀ ቤት ተፈናቅሎ በመጠለያ መሆን ህይወታቸውን እንዳመሰቃቀለው ወይዘሮ ቤዛዊት ገልጸዋል፡፡
የመሐል ሜዳ ነዋሪዎች እና ወጣቶች ያልተቋረጠ ድጋፍ ባይኖር ኖሮ ችግሩ ከዚህም ይከፋ ነበር ነው ያሉት፡፡ እስካሁን ባለው ሂደት ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እና ከማኅበራት ድጋፍ ቢደረግም ካለው ችግር እና ከተፈናቀለው ሕዝብ ቁጥር ጋር የሚመጣጠን እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
ከአጣዬ ከተማ በቅርብ ርቀት ከምትገኝ የገጠር አካባቢ እንደተፈናቀሉ እና እስካሁን ድረስ ስድስት ቤተሰቦቻቸው የት እንዳሉ እንኳን እንደማያውቁ የነገሩን ሌላው ተፈናቃይ ደግም አቶ ሰዒድ እንድሪስ ናቸው፡፡ በአካባቢው ሚሊሻ ውስጥ አባል እንደሆኑ የነገሩን አቶ ሰዒድ በአጣዬ ከተማ የተፈጠረው ውድመት ከመከሰቱ በፊት ግዳጅ ላይ እንዳሉ ቆስለው ሆስፒታል ነበሩ፡፡ የአጣዬ ከተማን ስርዓት አልበኞች እንዳልሆነች ሲያደርጓት ከሆስፒታል ሸሽተው መሐል ሜዳ እንደደረሱም ነግረውናል፡፡ መሐል ሜዳ ከደረሱ ሰባተኛ ቀን ቢሆናቸውም ቤተሰቦቻቸው የት እና በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ ግን እስካሁንም አያውቁም፡፡
በመሐል ሜዳ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ የመሐል ሜዳ ከተማ ነዋሪዎች እና ወጣቶቹ ሳይሰለቹ ምግብ በማብሰል፣ አልባሳት በማቅረብ እና ሌሎች የሰብዓዊ ድጋፍ በማድረግ እንደያዟቸው ገልጸዋል፡፡ ችግሩ በውስን ሕዝብ ድጋፍ እልባት የሚያገኝ ባለመሆኑ መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡ አልባሳት፣ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ፣ የህፃናት አልሚ ምግብ እና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ሠላም እንዲያረጋግጥላቸው ነው የተናገሩት፡፡
አፋጣኝ የሰብዓዊ ድጋፍ በወቅቱ ለማቅረብ ጥረት መደረጉን የገለፁት የሰሜን ሽዋ ዞን የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኅላፊ አቶ ወርቅአለማሁ ኮስትሬ ናቸው፡፡ ከተፈናቃዮች ብዛት እና ከነበረው የፀጥታ ችግር አንፃር በቂ ድጋፍ ተደራሽ አልሆነም ብለዋል፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት 253 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች እንዳሉ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ ተፈናቃዮችን በጊዜያዊነት የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ እና በቋሚነት ወደ ቀያቸው ለመመለስ የተለያዩ ጥረቶች እየተካሄዱ ነው ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
0
People Reached
31
Engagements
Boost Post
25
4 Comments
2 Shares
Like

Comment
Share
Previous articleበአማራ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተቋቋመ።
Next articleʺዓባይ የዘጋውን ዓባይ ይከፍተዋል “