በቻግኒ ራንች ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ይነሳ የነበረው የሰብዓዊ ድጋፍ ፍትሐዊት ጥያቄ መፈታቱን ተፈናቃዮች ገለጹ፡፡

176
በቻግኒ ራንች ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ይነሳ የነበረው የሰብዓዊ ድጋፍ ፍትሐዊት ጥያቄ መፈታቱን ተፈናቃዮች ገለጹ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 17/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከመተከል ዞን በማንነታቸው ምክንያት ተፈናቅለው በቻግኒ ራንች ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ዜጎች ያሉበትን ሁኔታና ሰብዓዊ ድጋፍ አስመልክቶ ተከታታይ ዘገባዎችን መስራቱ ይታወሳል፡፡ በዚህም ሰብዓዊ ድጋፉ የተደራሽነት እና የፍትሐዊነት ችግር እንዳለበት አንስተው ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅትም ችግሩ ተስተካክሎ ፍትሐዊ የሆነ ድጋፍ እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ችግሩ ሊስተካከል የቻለውም የአማራ ክልል አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትና እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ድጋፉን ማስተባበር የሚችል አዲስ ግብረኃይል አቋቁሞ ወደ ሥራ በመግባቱ ነው፡፡
ተፈናቃዮቹ “በፊት ድጋፍ እያለ በወቅቱ አይሰጠንም፤ ቢሰጠንም ፍትሐዊነት የጎደለው ነበር” ብለዋል፡፡ አሁን በተዋቀረው ግብረኀይል በአባልነት ስለተሳተፉበት የሚደርሳቸውን ድጋፍ በፍትሐዊነት እየተከፋፈሉ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በቻግኒ ራንች ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች የሰፈሩበት አካባቢ ለጎርፍ የተጋለጠ በመሆኑና ክረምት ሲገባ ለጉዳት ተጋላጭ ከመሆናቸው በፊት የቅድመ መከላከል ሥራ ሊሠራ እንደሚገባም ተፈናቃዮቹ ጠይቀዋል፡፡
በቻግኒ ጊዜያዊ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ የአስቸኳይ የአደጋ ምላሽ ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ አቶ ጌቴ ምሕረቴ አዲሱ የተቋቋመው ግብረኀይል ተፈናቃዮቹን በማወያየትና እነሱ ያመኑበትን አባላት በማካተት ሲነሱ የነበሩትን ቅሬታዎች መፍታት ተችሏል ብለዋል፡፡ “ማኅበረሰቡን አሳትፈን ከሠራን የማይፈታ ችግር የለም፤ በፊት እኔ አውቅልሃለው ነበር ብለን ሥንሠራ የነበረው፤ ይህ ትክክል አይደለም” ብለዋል አስተባባሪው፡፡ አሁን ግን የሚሠሩትን ሥራ ሁሉ የማኅበረሰቡን ተወካዮች በማሳተፍ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የጤና ባለሙያዎች በመጠለያ ጣቢያው ተመድበው ተፈናቃዮቹ የሕክምና አገልግሎት እያገኙ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ድጋፍ ሲያደርግ የነበረው ፕሮጀክት ስለወጣ የሕክምና አገልግሎቱ እንዳይቋረጥ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሠሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በመጪው ክረምት መጠለያ ጣቢያው ለጎርፍ ተጋላጭ በመሆኑ አደጋ እንዳይከሰት አማራጮችን በመፈለግ ችግሩን ለመከላከል እየተሠራ መሆኑን አቶ ጌቴ አስረድተዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የሕዝቦች ጥያቄ ከጎዳና ወደ ፓርላማ የሚገባበት፣ ሕዝባዊ ቅቡልነት ያለው መንግሥት የሚመሠረትበት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡
Next articleእንጅባራ ከተማ ሊገባ የነበረ ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ እና ጥይት በቁጥጥር ስር ማዋሉን የፋግታ ለኮማ ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ::