የመራጮች ምዝገባ መራዘሙን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

389

የመራጮች ምዝገባ መራዘሙን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 15/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው መርሃግብር መሰረት የመራጮች ምዝገባ ቀን ዛሬ እንደሚጠናቀቅ ይታወቃል። እስካሁን በተከናወነው የመራጮች ምዝገባ ሂደትም በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ የምዝገባው ሂደቶች በተለያየ ደረጃ ሲከናወኑ መቆየታቸውን አስታውቋል። ቦርዱ ለአብነትም በሶማሌ እና በአፋር ክልል የመራጮች ምዝገባ ዘግይቶ ሲጀመር በሌሎች ክልሎች ደግሞ ቀደም ብሎ ሲከናወን እንደነበር ጠቅሷል።

የመራጮች ምዝገባ በቀደመው ሳምንት ቦርዱ ካሳወቀበት ደረጃ በከፍተኛ ደረጃ የተሻሻለ ሲሆን የምርጫ ጣቢያዎች ያልተከፈቱባቸው የነበሩት የአፋር ብሔራዊ ክልል እና የሶማሌ ብሔራዊ ክልልም የምርጫ ጣቢዎች ተከፍተው የመራጮች ምዝገባን ማከናወን መጀመራቸውን ገልጿል። እስከ ሚያዝያ 14 /2013 ዓ.ም ድረስም 18 ሚሊዮን 427 ሺህ 239 ዜጎች የተመዘገቡ መሆኑንና በ41 ሺህ 659 ምርጫ ጣቢያዎች መራጮችን እየመዘገቡ እንደሚገኙ ቦርዱ በመግለጫው አብራርቷል ።

ቦርዱ የመራጮች ምዝገባ ቀን ማጠናቀቂያ ዛሬ መሆኑን ተከትሎ የሥራ ሂደቱንና ያጋጠሙትን ችግሮች መመርመሩን አስታውቋል። በዚህም መሰረት

1. የመራጮች ምዝገባ በግማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች ዘግይቶ በመጀመሩ
2. በጊዜው በተጀመረባቸውም ቦታዎች የመራጮች ምዝገባ መረጃዎች እጦት እና በሌሎች ምክንያቶች ለመመዝገብ ጊዜ በመውሰዱ
3. የመራጮች ምዝገባ ሊጠናቀቁ በቀሩት ጥቂት ቀናት በአንድ ምርጫ ጣቢያ 1 ሺህ 500 ሰው ብቻ መመዝገብ በመቻሉ የተነሳ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር በሚገኙ የተወሰኑ ምርጫ ጣቢያዎች ምዝገባ በመቋረጡ እና ተጨማሪ ምርጫ ጣቢያዎች በመክፈት ሂደት ክፍተት በመፈጠሩ ቦርዱ የመራጮች ምዝገባ እንዲራዘም መወሰኑን ገልጿል።

በመሆኑም
1. የመራጮች ምዝገባ እጅግ ዘግይቶ በጀመረባቸው በአፋር እና በሶማሌ ክልል የመራጮች ምዝገባ ለሶስት ሳምንት መራዘሙንና የመራጮች ምዝገባ ግንቦት 06 /2013 ዓ.ም የሚጠናቀቅ መሆኑ ተጠቅሷል።

2. የመራጮች ምዝገባ ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች በተስተጓጎለባቸው ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ለሁለት ሳምንት ተራዝሟል ይህም ማለት የመራጮች ምዝገባ ሚያዝያ 29 /2013 እንደሚጠናቀቅነው የተብራራው።

3. የመራጮች ምዝገባ እስካሁን ባልተጀመረባቸው እና የጸጥታ ችግር ባለባቸው ቦታዎች በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ወለጋ፣ ምስራቅ ወለጋ፣ ሆሮጉድሩ እና ቄለም ወለጋ የመራጮች ምዝገባን የማስጀመር እንቅስቃሴዎችን እየተደረገ ነው ብሏል።

በነዚህ ዞኖች
• አሊቦ – ሆሮ ጉድሩ
• ኮምቦልቻ- ሆሮ ጉድሩ
• ጊዳም – ሆሮ ጉድሩ
• አያና – ምስራቅ ወለጋ
• ገሊላ- ምስራቅ ወለጋ
• ቤጊ- ምእራብ ወለጋ
• ሰኞ ገበያ- ምእራብ ወለጋ የመራጮች ምዝገባ አሁንም የማይጀመር ሲሆን ከነዚህ ውጪ ባሉት ወረዳዎች የመራጮች ምዝገባን ለመጀመር የቁሳቁስ ስርጭት እየተከናወነ እና የአስፈጻሚዎች ስልጠናንም እየተሰጠ ይገኛል ብሏል ቦርዱ።

በተመሳሳይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከማሽ ዞን ከሰጎን ወረዳ ውጪ የመራጮች ምዝገባን ለማካሄድ የቁሳቁስ ስርጭት እና የአስፈጻሚዎች ስልጠና እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሷል።

በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን እንዲሁም በአማራ ክልል በኦሮሚያ ልዩ ዞን ያሉ የምርጫ ስራዎች የቆመባቸው ቦታዎችን ጨምሮ እንደየሁኔታው በነዚህ ቦታዎች የመራጮች ምዝገባ የሚጀመርበትን ሁኔታ እና ቀናት ቦርዱ እንደሚያሳውቅም ገልጿል።

4. 1 ሺህ 500 ሰዎቸን መዝግበው በጨረሱ ምርጫ ጣቢያዎች ተጨማሪ ንዑስ ምርጫ ጣቢያዎችን መክፈት የሚቀጥል ይሆናል ብሏል።

በዚህም መሰረት ፓለቲካ ፓርቲዎች፣ መገናኛ ብዙኀንና ሲቪል ማህበራት የመራጮች ምዝገባን ለማበረታታ የሚያደርጉትን ጥረት እንዲቀጥሉ፤ ምርጫ አስፈጻሚዎችም የመራጮች ምዝገባን እንዲያከናውኑ ነው ቦርዱ ያሳሰበው። መረጃው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleሕዝብ ላነሳቸው ጥያቄዎች መንግሥት ምላሽ እንዲሰጥ እና አጥፊዎች ለሕግ እንዲቀርቡ የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠየቀ፡፡
Next articleመንግሥት ሀገራዊ ህልውናን አደጋ ላይ ለመጣል የሚሞክሩ የውስጥና የውጭ ፀረ ሰላም ኃይሎችን በምንም አይነት ሁኔታ እንደማይታገስ የደህንነትና ጸጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ።