
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እና ኦሮሞ ብሄረሰብ አሥተዳደር ባሉ ከተሞች የደረሰውን ጥቃት ለመቀልበስ በአካባቢው የተቋቋመ ኮማንድ ፖስት የተቀናጀ ሥራ እያከናወነ መሆኑ ተገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 15/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባሉ ከተሞች የደረሰውን ጥቃት ለመቀልበስ በአካባቢው የተቋቋመ ኮማንድ ፖስት የተቀናጀ ሥራ እያከናወነ መሆኑን የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ገልጿል፡፡ በአካባቢው አንጻራዊ ሠላም እየተረጋገጠ መምጣቱንም ነው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሠራዊት ግንባታ ሥራዎች ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ በሰጡት መግለጫ ያስታወቁት፡፡
በሀገሪቱ ወቅታዊ የሰላም ጉዳይ ዙሪያ ዛሬ ማብራሪያ የሰጡት ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳዳር አካባቢዎች ከሰሞኑ በተቃጣው የሽብር ጥቃት እንዲሁም የሕወሃት ርዝራዦች ከሀገር ለመውጣት ያደረጉት ሙከራ ለማክሸፍ በተከናወኑ ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርገዋል፡፡
ከሀገር ለመውጣት ከሞከሩት መካከል አብዛኛዎቹ መደምሰሳቸውን እና የተወሰኑት ወደኋላ ተመልሰው ሸለቆ ውስጥ መደበቃቸውን በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡ ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ ቅሪቶቹ የሕወሃት ርዝራዦች መታወቂያ በማዘጋጀት እና ስማቸውን በሌላ ማንነት በመቀየር በአማራ ክልል አቋርጠው ወደ ሱዳን ለመውጣት ያደረጉት ሙከራ መክሸፉን ገልጸዋል፡፡ ቡድኑ ከሀገር ለመሸሽ ያደረገው ጥረት ሁሉ የተዘጋ እና ያለቀለት ደረጃ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ሌተናል ጀኔራል ባጫ በአጣዬ እና አካባቢው ጥቃት ተፈፀሞባቸው የሸሹ ዜጎችን ወደነበሩበት ለመመለስ ኮማንድ ፖስቱ በቅንጅት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፤ ይህን ተከትሎም አካባቢው ወደቀድሞ ሠላሙ እየተመለሰ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በሕግ የማስከበር ዘመቻው ሠራዊቱ ለሀገር ሲል ከባድ መስዋእትነት እየከፈለ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የመከላከያ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ናቸው፡፡ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የጥፋት ኃይሎች በሕዝቡ ላይ የሚያደርሱትን ሰቆቃ ለመታደግ መከላከያ ሠራዊት ሀገራዊ ተልእኮውን ይዞ የህይወት መስዋእትነት በመክፈል ጭምር መጠነ ሰፊ ግዳጆችን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
በአማራ ክልል ሦስቱም ዞኖች የተቋቋመው ኮማንድ ፓስት በአምስት ወረዳዎች እና በሦስት ከተማ አሥተዳደሮች የተፈናቀሉትን የመመለስ፣ መሥተዳደሮቹን መልሶ የማደራጀት፣ ወንጀለኞችን አድኖ የመያዝ እና የሰብዓዊ ድጋፎችን እያስተባበሩ መሆኑን ኮሎኔል ጌትነት ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ጋሻው ፋንታሁን – ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ