
በዚህ ወቅት ከገጠመው ችግር ለመውጣት የሰከነ ውይይት እና በሥነ ምግባር የተገራ የሥነ ተግባቦት አውድ መፍጠር
እንደሚያስፈልግ ተገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 14/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ቀውስ የሕይወት መጥፋት፣ የንብረት መውደም፣ የማኅበረሰቡን የኑሮ ሁኔታና
የተቋማትን የእለት ከእለት የሥራ እንቅስቃሴ ያደናቅፋል፡፡ በሕዝብ ወይም በተቋማት ላይ ችግር በሚፈጠርበት ጊዜ ችግሩን
ለመፍታት እና ጉዳቱን ለመቀነስ በሰከነ እና በመደማመጥ ላይ የተመሰረተ ተግባቦት እና የመረጃ ልውውጥ ያስፈልጋል፡፡
በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ሥነ ተግባቦት መምህር አደም ጫኔ (ዶክተር) አሁን ሀገሪቱ ካለችበት ችግር ለመውጣት
የመንግሥት፣ የሕዝብ፣ የማኅበራዊ አንቂዎች እና የመገናኛ ብዙኀን ተግባቦት ምን መምሰል እንዳለበት ሃሳብ ሰጥተዋል፡፡
ዶክተር አደም በቀውስ ወቅት የመንግሥት፣ የማኅበረሰቡ፣ የብዙኃን መገናኛ ተቋማት እና የማኅበረሰብ አንቂዎች የሰከነ
ተግባቦት ለሀገር ሕልውና ፋይዳው የጎላ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ዶክተር አደም እንዳሉት ብዙኃን መገናኛዎች ሀገራዊ አንድነትን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው ሊዘግቡ ይገባል፤
የአጥቂነት እና የተጠቂነት ዘገባዎችን ከማቅረብ ወጥተው በችግሩ ምንጭ እና መፍትሔ ላይ ማተኮር እንደሚገባም መክረዋል፡፡
ከማኅበራዊ አንቂ ተጽእኖ በመላቀቅም ትክክለኛ የጋዜጠኝነት መርህ ላይ መቆም እንደሚያስፈልግም ነው ዶክተር አደም
የገለጹት፡፡
መንግሥትም በቀውስ ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለበት ምክረ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡ የመንግሥት ተቀዳሚ ዓላማ የዜጎችን
በሕይወት የመኖር መብት መጠበቅ እስከ ሆነ ድረስ ለሚፈጠሩ ችግሮች “ውጫዊ ከማድረግ ወጥቶ” በቀጣይ እንዳይደገሙ
ትኩረት አድርጎ መሥራት እንዳለበት መክረዋል፡፡
መግለጫዎች ሲሰጡም ኀላፊነት በተሞላበት መንገድ መሆን አለበት ነው ያሉት፡፡ ለሚፈጠሩ ችግሮች ፈጣን፣ ወቅቱን የጠበቀ
ምላሽ መስጠት እንደሚገባም አንስተዋል፡፡
የቀውስ ጊዜ ተግባቦት የአስቸኳይ ጊዜ አስተዳደር ዋና አካል እንዲሆን መንግሥት ትኩረት መስጠት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡
የማኅበራዊ ትስስር መረቦች በአብዛኛው በሚፈጠሩ ችግሮች መፍትሔ ላይ መሥራት ሲገባቸው ችግር አቀጣጣይ፣ ውጥረት
እንጋሽ፣ ከፋፋይ እና ተራ የሆኑ መረጃዎች የሚቀርቡበት መድረክ መሆን እንደሌለበት አንስተዋል፡፡ ለድምጽ አልባዎች ድምጽ
የሆኑ፣ ለሚፈጠሩ ችግሮች መንግሥት ትኩረት እንዲሰጥ የሚተጉ ማኅበራዊ አንቂዎች እንዳሉም ጠቅሰዋል፡፡
ማኅበረሰቡም በህይዎት ዘይቤው ነገሮችን መርጦ እንደሚያከናውነው ሁሉ በማኅበራዊ የመገናኛ ትስስሮች የሚለቀቁ
መረጃዎችንም ሚዛናዊነት እና ትክክለኛነታቸውን ማጣራት እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡
የሕዝቦችን ግንኙነት እንዲጠናከር የሚተጉ እና የተዛባ ሀሳብ የሚያራምዱትን ደግሞ ማስተካከል የሚችሉ የማኅበረሰብ
አንቂዎች ሊኖሩ እንደሚገባም መክረዋል፡፡
በዚህ ወቅት ከገጠመው ችግር ለመውጣትም የሰከነ ውይይት እና በሥነ ምግባር የተገራ የሥነ ተግባቦት አውድ መፍጠር
እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡ መግባባት፣ መደማመጥ እና ማኅበራዊ ኀላፊነትን መሸከም የሚያስችል አቅም መገንባት
ይገባልም ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m