
የተፈናቀሉ ዜጎችን የመደገፍ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ የአማራ ክልል አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትና እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 14/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ክልሉ በየወሩ ከ60 ሺህ ኩንታል በላይ እህል ለተፈናቃዮች ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡ የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኢያሱ መስፍን ለአሚኮ እንዳሉት ከሰሞኑ በሰሜን ሸዋ ዞን የተፈጠረውን ችግር ሳይጨምር ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ 495 ሺህ ዜጎች ተፈናቅለዋል፡፡ በቅርቡ በአጣዬ በደረሰው ጥቃት ደግሞ ከ253 ሺህ በላይ ዜጎች ለችግር ተዳርገዋል፡፡ የንጹሃን ዜጎችን ሞትና መፈናቀል ሰብዓዊ ፍጡር የሆነ ሁሉ ማውገዝ እንደሚገባውም ተናግረዋል፡፡
በሰሜን ሸዋ ዞን በደረሰው ጥቃት የአካባቢው ሕዝብ ያደረገውን ድጋፍ ኃላፊው አድንቀዋል፡፡ ከኀብረተሰቡ ባለፈ ለተፈናቀሉ ወገኖች ረጅ ድርጅቶችና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ከዞኑ ተጠሪ ተቋም ጋር በመሆን ድጋፍ አድርገዋል ነው ያሉት፡፡ የክልሉ መንግሥትም ድጋፍ ማድጉን ነው የተናገሩት፡፡
ሰላሙ ወደ ነበረበት ተመልሶ ዜጎች እስኪቋቋሙ ድረስ ድጋፉ ይቀጥላልም ብለዋል፡፡
ኃላፊው ሁሉም በሚችለው አቅም ለሠላም ዘብ መቆም ይገባል፤ እርዳታ ከድህነት የማያሻግር በመሆኑም ጸጥታውን በማስጠበቅ የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ