
አማራ እየገጠሙት ያሉ ፈተናዎችን ለማለፍ ኀብረተሰቡ መረዳዳትና መደጋገፍ እንደሚገባው የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 13/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ማንነት ተኮር ጥቃት ለመቀልበስ ኅብረተሰቡ በተለይ ወጣቱ መደማመጥና ማስተዋል እንደሚጠበቅበት አሚኮ ያነጋገራቸው የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ለአሚኮ አስተያየት ከሰጡ ነዋሪዎች መካከል ወጣት ሳሙኤል ጌታሁን ችግሮችን ስሜታዊ በሆነ መልኩ መጋፈጥ እንደማይገባ ተናግሯል። እንደ ሀገር ብዙ አስቸጋሪ ጊዜዎችን አሳልፈናል፤ በተለይ አሁን ወጣቱ በየአካባቢው ተደራጅቶ በመጠበቅ የፀጥታ አካላት ሊያግዝ እንደሚገባ ተናግሯል፡፡
አሁን እየገጠመ ያለውን ክልላዊና ሀገራዊ ችግር መሻገር የሚቻለው በመረዳዳት ነው ያለው ደግሞ አቶ ክንድዬ መኮንን ናቸው። ማኅበረሰቡና የጸጥታ አካላት ተናበው በጋራ መሥራት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
አቶ መሐመድ ፋንታሁን የተባሉ ነዋሪ ደግሞ በዚህ ወቅት ከሁሉም በፊት የሕዝብ አንድነት ሊኖር እንደሚገባ ነው የገለጹት። ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን በጋራ ሆኖ መመከት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
ወይዘሪት ይህቺዓለም ታምር በየአካባቢው የሚስተዋለውን የሰላም እጦት በተረጋጋ ሁኔታ ማጤን እንደሚያስፈልግ ገልጻለች። ወጣቱን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኘው የማኅበረሰብ ክፍል አካባቢውን ነቅቶ በመጠበቅ ሊደጋገፍ እንደሚገባ ተናግራለች።
ወጣት በለጠ ወዳጅነው ደግሞ የወቅቱን ፈተና ለማለፍ የኅብረተሰቡንና የጸጥታ አካላትን ጥምረት እንደሚጠይቅ ጠቁሟል። በክልሉ የተፈጠረውን የሰላም እጦት ለማረጋጋት ከወጣቶች፣ ከማኅበረሰቡ፣ ከጸጥታ አካላትና ሌሎችንም ያካተተ አደረጃጀት መቋቋም አለበት ነው ያለው።
በየአካባቢው የተጎዱ ወገኖችን መርዳት እንደሚያስፈልግም ተናግሯል፡፡
ዘጋቢ፡- ብሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ