በአማራ ላይ የተሠራውን የሀሰት ትርክት ለመቀየር መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባው የፖለቲካ ምሁር ተናገሩ፡፡

299
በአማራ ላይ የተሠራውን የሀሰት ትርክት ለመቀየር መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባው የፖለቲካ ምሁር ተናገሩ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 13/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት የአማራ ሕዝብ በማንነቱ ብቻ ሲገደል፣ ሲሳደድ፣ ሲፈናቀልና ሀብት ንብረቱ ሲወድም ቆይቷል፡፡ በተለይ ለ27 ዓመታት ሀገርን ሲያስተዳደር የነበረው ትህነግ የአማራ ሕዝብን የማይገልጽ ትርክት በመዝራት የአማራን ሕዝብ ለተለያየ እንግልት ዳርጎታል፡፡
አሁን ላይ በአማራ ላይ እየደረሰ ያለዉ ጥቃት ምክንያቱ ምን እንደሆነና ጥቃቱን እንዴት ማስቆም እንደሚቻል በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ዶክተር ደጉ አስረስን ጠይቀናል፡፡ በአማራው ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት ምክንያቱን በሁለት መንገድ ተመልክተውታል፡፡
አንደኛው በሀሰት ትርክት አማራ ገዢ መደብ እንደነበረ፣ ጨቋኝ ተደርጎ መሳሉ አማራን ለተለያዩ ጉዳቶች እየዳረጉት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ወደ ሥልጣን የመጡ ኀይሎችም ይህንን የተሳሳተ ትርክት ሲጠቀሙበት እንደቆዩ ምሁሩ ጠቁመዋል፡፡ የፖለቲካ ኀይሎችም የሀሰት ትርክቱን ለዓላማቸው ኾን ብለው ይጠቀሙበታል እንጂ በኢትዮጵያ ታሪክ አንድ ገዥ መደብ ብቻዉን ሀገር እንዳልመራ ያውቁታል ነው ያሉት ምሁሩ፡፡ አማራ እንደ ሌሎች ሕዝቦች ሀገርን ሲገነባ የኖረ እንጂ በተለየ መንገድ የተጠቀመው ነገር አንደሌለም አስገንዝበዋል፡፡
ዶክተር ደጉ በሁለተኛነት ያስቀመጡት ሀሳብ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚፈልጉ የውጪም ሆነ የውስጥ ኀይሎች ከሚያከናወኑት ተግባር ውስጥ አንዱ አማራውን ማዳከም ነው ብለዋል፡፡
ምሁሩ ሀገራዊ አንድነትን ለማምጣት መፍትሔ የሚሏቸዉን ምክረሀሳቦችም ሰንዝረዋል፡፡ በተለይ መንግሥት በአማራው ላይ ሲነዛ የነበረውን የሀሰት ትርክቶች ትክክል አለመሆናቸውንና ሀገር ወዳድ ሕዝብ መሆኑን ማሳወቅ፣ ሕገ መንግሥቱን በማሻሻልና የትምህርት ሥርዓቱን በመከለስ አሁን ላለው ትውልድ ማስተማር ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡ በሕዝቦች መካከል የምክክር መድረክና ሠላማዊ ግንኙነቶች እንዲኖሩ ማድረግም ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- ብሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleወጣቶች በመደማመጥ የክልሉን ሰላም የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ጠየቀ።
Next articleለኢትዮጵያ ዘብ እንቁም በሚል የኢትዮጵያዊያን ግብረ ኃይል በአውሮፓ ተቋቋመ፡፡