
ከሰርጎ ገቦች ጥቃት አካባቢያቸውን እየጠበቁ መሆኑን የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 11/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ነዋሪዎች በሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬና ሸዋሮቢት አካባቢዎች ላይ የደረሰው ጉዳት እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡ ጥቃቱ በአካባቢያቸውም እንዳይከሰት አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ሊደርስ የሚችልን ጥቃትም ለመከላከል መደራጀታቸውን ነው የነገሩን፡፡
የወረዳው ነዋሪ አቶ ዮሐንስ ተዘራ በአጣዬና ሸዋሮቢት የደረሰው ጉዳት እንዳሳዘናቸውና አካባቢያቸውን ከማንኛውም ጥቃት ለመከላከል ኀብረተሰቡ አደረጃጀት በመፍጠር እየጠበቀ ነው ብለዋል፡፡
አሚኮ ያነጋገራቸው ሌላው አቶ ሰለሞን ኀይሌ እንዳሉት በአጣየ እና በሌሎችም አካባቢዎች የተከሰተውን ጉዳት ለማውገዝ ሰው መሆን በቂ ነው፡፡ አንድነት ኀይል ነው፣ ኅብረተሰቡ አንድ በመሆን የሚመጣን ጥቃት በጋራ ሊወጣ ይገባል ነው ያሉት፡፡ ለዚህም የአካባቢው ማኅበረሰብ መረጃ በመለዋወጥ በንቃት ጸጥታዉን እየተከታተለ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ለዚህም በቂ የሥነልቦና ዝግጅት አለ ብለዋል፡፡
በእምነት ተቋማት አካባቢ ያለው ጥበቃ እጅግ የተጠናከረ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡ በሰርጎ ገቦች በአካባቢው ያሉ መሰረተ ልማቶች ጥቃት እንዳይደርስባቸው ጥበቃ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ ማኅበረሰቡ ለጸጥታ መዋቅሩ አጋዥ በመሆን እየሠራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡
የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ እና የሰላም እና ሕዝብ ደኅንነት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሳሙኤል ብርሃኔ የአካባቢው ማኅበረሰብ የጸረ ሰላም ኀይሎችን ሴራ እንዲረዳ እና መከላከል እንዲችል አስፈላጊው ግንዛቤ እየተፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ማኅበረሰቡ ወዘ ልውጥ ሲያይ አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ መረጃ እንዲሰጥ እና ከመንግሥት ጋር በጋራ እንዲሠራ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አካባቢው ከኦሮሚያ ክልል የሚዋሰን በመሆኑ ጸረ ሰላም ኀይሎች የሰርጎ ገብ ጥቃት በመፈጸም ሁለቱን ወንድማማች ሕዝብ እንዳያጋጩ አስፈላጊውን ክትትልና ቅኝት በማድረግ እየተሠራ እንደሆነ ነው አቶ ሳሙኤል የነገሩን፡፡ ከአዋሳኝ አካባቢ የኀብረተሰብ መሪዎች ጋር መረጃ በመለዋወጥ ቀጣናውን በጋራ መጠበቅ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር መደረጉንም አንስተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ምስጋናው ብርሃኔ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ