
የአማራ ክልልን ደኅንነት ለመጠበቅ ኅብረተሰቡ ከመቼዉም ጊዜ በላይ ሊደራጅ እንደሚገባ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 10/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰተ ባለው የጸጥታ ችግር ዙሪያ አሚኮ
አንዳንድ የክልሉ ነዋሪዎችን አነጋግሯል።
ወይዘሮ አገርነሽ ፈንታው የሚኖሩት በደሴ ከተማ ነው። የክልሉን ሠላም የማይፈልጉ ኀይሎች ሕዝቡን እየጨፈጨፉ፣ ሀብትና
ንብረት እያወደሙ ብሎም እያፈናቀሉ ስለሆነ ኅብረተሰቡ አካባቢዉን በንቃት መጠበቅ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
“የሠላም አዋኪዎቹ ይዘዉት የሚመጡትን አጀንዳ ኅብረተሰቡ በግልጽ መለየትና ለጸጥታ አካላት ማጋለጥ አለበት” ነው ያሉት
ወይዘሮ አገርነሽ። ኅብረተሰቡ ለዘመናት በባሕል፣ በጋብቻና በሌሎችም የተጋመደ በመሆኑ መነጣጠል እንደማይቻልም
ተናግረዋል። “ሲፈልጋቸው በብሔር አልያም ደግሞ በሃይማኖት አጀንዳ ይዘው የሚመጡ ሠላም ጠል ኀይሎችን ኅብረተሰቡ
በመደራጀት ሊከላከላቸው ይገባል” ብለዋል።
መንግሥት በነዚህ ኀይሎች ላይ ጥብቅ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
ወጣት ኤርምያስ ገዳሙ ነዋሪነቱ በባሕር ዳር ከተማ ነው። የሠላም እጦት ሲከሰት ፈጣን እርምጃ በመውሰድ ላይ ድክመት
ስለሚታይ መታረም አለበት ነው ያለው።
“የክልሉ ሕዝብ የሚሰጠዉን ተልዕኮ በሚያኮራ መልኩ መፈጸም ስለሚችል መሪው ሕዝቡን የማደራጀት ሥራ የመሥራት ኀላፊነት
አለበት” ብሏል።
በደቡብ ጎንደር ዞን የደራ ወረዳ ነዋሪ አቶ አዱኛ በየነ የሠላም ችግር የሚሆኑ መንስኤዎችን በመለየት የሕዝብ ለሕዝብ ውይይት
መደረግ አለበትም ብለዋል። ለክልሉም ሆነ ለሀገር አንድነት ሲባል ኅብረተሰቡ ተደራጅቶ አካባቢውን በንቃት መጠበቅ አለበት
ነው ያሉት።
አቶ አዱኛ በሰጡት አስተያየት “የክልሉ ወጣት ለሚሰጠው ተልዕኮ ወደኋላ ስለማይል በወጣቱ ላይ መሥራት ያስፈልጋል”
ብለዋል። መንግሥት የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ተግባራዊ የሆነ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል፡፡
በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ቲሊሊ ከተማ ነዋሪ መምህር ከፍያለው ታምሩ የሕዝቡን አንድነት የማስጠበቅ ሥራ ተጠናክሮ
መሠራት እንዳለበት ተናግረዋል። “የክልሉ ሕዝብ አንድነቱን የሚጠብቅበት ወቅት ላይ እንገኛለን። አንድነቱን የጠበቀ ማኅበረሰብ
በቀላሉ ሊደፈር አይችልም” ብለዋል። ሀገሪቱ የምትገኝበትን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ የሥራ ኀላፊዎች ለማኅበረሰቡ በቂ መረጃ
ሊሰጡ እንደሚገባም መምህር ከፍያለው አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፡- ብሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m