ግብጽና ሱዳን በዓባይ ተፋሰስ በሚከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ሥራዎች ሊሳተፉ እንደሚገባ ባለሙያዎች ገለጹ፡፡

349
ግብጽና ሱዳን በዓባይ ተፋሰስ በሚከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ሥራዎች ሊሳተፉ እንደሚገባ ባለሙያዎች ገለጹ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 08/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ዘላቂ የውኃ ፍሰት ለማስጠበቅ የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት በሚያከናውኗቸው የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራዎች ላይ ግብጽና ሱዳን ሊሳተፉ እንደሚገባ ባለሙያዎች አመላከቱ፡፡ የናይል ተፋሰስ ሀገራት ድንበር ዘለል ወንዞችን በጋራ ለማልማትና ለመጠቀም የተለያዩ ውይይቶችን አድርገዋል፡፡ ከተደረጉት ውይይቶች ውስጥ ደግሞ የተፋሰሱን አካባቢ ደኖች መጠበቅ እና የተፈጥሮ ሀብት ሥራ መሥራት አንዱ ነው፡፡
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ሰይፉ አድማሱ (ዶክተር) ግብጽ በግትርነቷ ብትጸናም ሱዳን ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ እንደምትጠቀም በመገንዘብ በተለያየ ጊዜ ድጋፏን ስታሳይ እንደነበር አንስተዋል፡፡ ይሁን እንጅ በሱዳን የተካሄደውን የሥርዓት ለውጥ ተከትሎ ሱዳን የግብጽን አቋም በመጋራት የታላቁን የሕዳሴ ግድብ ሁለተኛውን ዙር ውኃ ሙሌት ተቃውማለች፡፡
ምሁሩ እንዳሉት ግብጽ በዓባይ ተፋሰስ ላይ የምታነሳው ጥያቄ ሳይንሳዊ እና ፍትሐዊነት ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡ በአካባቢው ኀያልነቷን በማስጠበቅ የዓባይን ውኃ ያለማንም ተገዳዳሪነት በበላይነት ተቆጣጥሮ ለመጠቀም ካላት ፍላጎት የመነጨ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ይህንም ከጥንት ጀምሮ ስትከተለው መቆየቷን እና ወደ ፊትም ለማስቀጠል ካላት ፍላጎት የተነሳ ነው ብለዋል፡፡
የተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት ሊረጋገጥ የሚችለው ኢትዮጵያ በዓባይ ተፋሰስ በምታከናውናቸው ማንኛውም የተፈጥሮ ሀብት ልማት ላይ ሲሳተፉና ግብጽ የምታካሂደው የሴራ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ቆሞ በጋራ የመልማት ስምምነት ላይ ሲደረስ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ 86 በመቶ የሚሆነውን የዓባይ ውኃ አመንጭ እንደመሆኗ የውኃውን የተፈጥሮ ፍሰት ለማስቀጠል የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ኢትዮጵያ በምታከናውናቸው የተፈጥሮ ሃብት ሥራዎች ላይ ሊሳተፉ እንደሚገባም ምሁሩ አስገንዝበዋል፡፡
ኢትዮጵያም በተፋሰሱ በምታከናውነው የተፈጥሮ ሀብት ሥራ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት እንዲሳተፉ ትኩረት አድርጋ መሥራት እንዳለባት አሰገንዝበዋል፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃ እና አጠቃቀም ተወካይ ዳይሬክተር እስመለዓለም ምሕረት እንዳሉት የዓባይ፣ ተከዜ እና አዋሽ ተፋሰሶችን መሰረት ያደረገ የተፈጥሮ ኃብት ልማት ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡ በተለይም ደግሞ ግድቦች በሚገኙበት አካባቢ የተፈጥሮ ሃብት ሥራው ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሀገሪቱ ከፍተኛ ወጭ ታወጣለች። በዚህ ዓመት ብቻ ማኅበረሰቡ ለተፈጥሮ ሀብት ሥራ ያወጣው ወጭ በገንዘብ ሲተመን ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚሆን አንስተዋል፡፡
የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት የሚሠሩት የተፈጥሮ ሃብት ሥራ ጥቅም ለታችኛው ተፋሰስ ጭምር መሆኑን የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ተረድተው በተፈጥሮ ሀብት ሥራ መሳተፍ እንዳለባቸው ተወካይ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በጮቄ፣ ጉና፣ ሰሜን ሸዋ እና ደቡብ ወሎ ዞኖች ከፍተኛ ቦታዎች ጥናቶች በምሁራን እየተደረጉ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡ ይህም የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የውኃ ፍሰቱ ሳይቆራረጥ ዓመቱን ሙሉ የተሻለ ውኃ እንዲያገኙ ያግዛል ብለዋል፡፡ ደለል በማስቀረት ንጹህ ውኃ ብቻ እንዲደርሳቸው ያደርጋል፡፡
መንግሥት በቀጣይ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራው ላይ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ጭምር እንዲሳተፉ ትልቅ ሥራ እንደሚጠብቀውም አሳስበዋል፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ሚዲያ ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ኃይሉ አብርሃም እንዳሉት የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት ግድቡ ከመጀመሩ አስቀድሞ ድንበር ዘለል ወንዞችን በጋራ ለማልማትና ለመጠቀም ውይይቶች አድርገዋል፡፡
የተፋሰሱን አካባቢ ደኖች መጠበቅ እና የተፈጥሮ ሀብት ሥራ መሥራት ደግሞ አንዱ ነው፡፡ ኢትዮጵያም ይህንን ተገንዝባ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ባለፉት ዓመታት የተፋሰስ ልማት ሥራ ስታከናውን ቆይታለች። በዚህም ባለፉት ዓመታት እንደ ሀገር ለተፋሰስ ልማት የተሠራው ሥራ በገንዘብ ሲተመን 120 ቢሊዮን ብር የሚገመት ጉልበት ለአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ ውሏል ብለዋል፡፡ በቀጣይም በተጠናና በሳይንስ ተደግፎ የተፋሰስ ሥራን ለመሥራት ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ውውይት መደረጉንም ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ ተፋሰሶችን እያለማች ቢሆንም ግብጽና ሱዳን የተፈጥሮውን ውኃ ያለምንም ከልካይነት በበላይነት መቆጣጠር እንጅ ሀሳቡን ሊቀበሉት አለመቻላቸውን አንስተዋል፡፡ በመሆኑም የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የተፈጥሮ ፍሰቱን የጠበቀ ውኃ እንዲያገኙ በጋራ ተጠቃሚነትን ሊያረጋግጥ በሚችል የልማት ሥራዎች ላይ መሳተፍ እንዳለባቸው ነው አቶ ኃይሉ የጠቆሙት፡፡
በተፋሰሱ ላይ የሚሠሩ ተፈጥሮ ሀብት ሥራዎች ሱዳን ደለል ለማስጠረግ በየዓመቱ የምታወጣውን ከ20 እስከ 50 ሚሊዮን ዶላር ያስቀራል፤ 11 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ አስዋን ላይ በትነት የሚባክነውን ውኃ ይቆጥባል፡፡
ግብጽ ሰፊ የከርሰ ምድር ውኃ ያላት፣ ቀይ ባሕር እና ሜዲትራንያን ባሕርን በቴክኖሎጅ በማጣራት የመጠቀም እድል ያላት በመሆኗ ዓባይ የሕልውናዋ ጉዳይ የሚሆነው ለግብጽ ሳይሆን ለኢትዮጵያ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleለ300 ዜጎች የሥራ እድል የሚፈጥረው ብራስ ጋርመንት በቅርቡ ወደ ምርት ይገባል፡፡
Next articleዜጎች የምርጫ ካርድ ወሰደው ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን እንዲጠቀሙና ነጻ እና ፍትሐዊ ምርጫ እንዲካሄድ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ፡፡