
ለ300 ዜጎች የሥራ እድል የሚፈጥረው ብራስ ጋርመንት በቅርቡ ወደ ምርት ይገባል፡፡
በደብረ ታቦር ከተማ አስተዳደር የተገነባው ብራስ ጋርመንትና ቴክስታይል በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገባ ታውቋል፡፡ መታገስ አዱኛው ብራስ ጋርመንትና ቴክስታይል ድርጅት ተዋካይ እና የሕግ አማካሪ ፈቃደ መኮንን ለአሚኮ እንዳሉት ድርጅቱ በአዲስ አበባ ከ10 ዓመታት በላይ ሠርቷል፡፡ ይህን በማስፋት በ2011 ዓ.ም በደብረ ታቦር ከተማ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
በደብረ ታቦር ከተማ የተገነባው ጋርመንት በኀይል አቅርቦት ችግር ምክንያት መዘግየቱንም ተናግረዋል፡፡ በመታገስ አዱኛው ብራስ ጋርመንትና ቴክስታይል ድርጅት 126 ማሽኖች ገብተው ለሥራ ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ብራስ ጋርመንቱ ሠራተኞችን እየቀጠረ መሆኑንና አሰልጥኖ ወደ ሥራ እንደሚገባም አስታውቀዋል፡፡
ለ300 ዜጎች የሥራ እድል ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ነው የተናገሩት፡፡ ከአንድ ወር በኋላ ወደ ምርት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ ማሽኖች ከተጨመሩ እስከ 500 የሚደርሱ ሠራተኞችን መቅጠር እንደሚቻልም ገልጸዋል፡፡ ለዚሕም ማስፋፋያ መጠየቃቸውን ነው ያስታወቁት፡፡ በደብረ ታቦር ከተማ የብራስ የጋርመንቱ ወደሥራ መግባት ለሥራ እድል ፈጠራ፣ ለኢንቨስትመንት መነቃቃትና አካባቢው የኢንዱስትሪ ማዕከል እንዲሆን እድል ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡
አካባቢው የኢንዱስትሪ ሥፍራ እንዲሆንም ከብራስ ጋርመንቱ በተጨማሪ በሌሎች ዘርፎች ላይ ለመሠማራት ጥያቄ ማቅረባቸውን አንስተዋል፡፡ የሆቴል ቱሪዝምን ጨምሮ በሌሎች ኢንቨስትመንቶች እንደሚሳተፉ ነው የተናሩት፡፡ ደብረ ታቦር ከተማን የምርት ማዕከል ለማድረግ የሚያስችል ዕቅድ እንዳላቸውም ጠቅሰዋል፡፡ ጋርመንቱ በአዲስ አበባ 600 ሠራተኞች እንዳሉትም አስታውቀዋል፡፡ ባለሀብቶቹ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሌሎች የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለመተግበር እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ ለኢንቨስትመንት ቦታ የማቅረብ ችግር እንዳለበት ነው የተናሩት፡፡ በቶሎ ወደ ሥራ መግባት ለሚችሉ ባለሀብቶች ቦታ መስጠት እንደሚገባውም ነው የገለፁት፡፡ በከተማዋ ያለው የቦታ አሰጣጥ ኢንዱስትሪን ታሳቢ ያደረገ አለመሆኑንም ነግረውናል፡፡
የደብረታቦር ከተማ አስተደዳደር ኢንዱስትና ኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ታዘባቸው ፈንታሁን ወደማምረት የሚገቡትን ፕሮጀክቶች የማስፋፊያ ንድፋቸውን ገምግመን ነው ማስፋፊያ የምንሰጠው ብለዋል፡፡ የመታገስ ብራስ ጋርመንትንም የማስፋፊያ ንድፉን አይተን እንሰጣለን፤ ጥያቄዎችንም እንመልሳለን ነው ያሉት፡፡
የከተማዋን እድገት ታሳቢ ያላደረጉ የቦታ አሰጣጥ ችግሮች እንደነበሩ ያነሱት ኀላፊው አሁን ላይ ግን እድገቷን ታሳቢ ያደረጉ የኢንቨስትመንት ቦታዎችን ማመቻቸታቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ቀጣይ የሚኖሩ የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ቦታዎችም እድገቷን ታሳቢ ያደረጉ እንደሚሆኑ ነው ያስረዱት፡፡
በከተማ አስተዳደሩ 65 ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ያነሱት ኀላፊው 9ኙ ፕሮጀክቶች ማምረት የጀመሩ ናቸው ብለዋል፡፡ ሁለት ፕሮጀክቶች ደግሞ በቅርቡ ሥራ ይጀምራሉ ነው ያሉት፡፡
በከተማ አስተዳደሩ የኢንቨስትመንት ቦታ ወስደው ወደ ልማት ያልገቡ አራት ባለሀብቶች ቦታቸው መነጠቃቸውንም አስታውቀዋል፡፡ በከተማ አስተዳደሩ የኢንቨስትመንት ቦታ ወስደው ወደ ሥራ ያልገቡት በመንግሥት ወይስ በራሳቸው ችግር የሚለውን በመለየት ነው ባለሃብቶቹ ቦታውን የተነጠቁት ብለዋል፡፡
16 ባለሀብቶች ላይ ማስጠንቀቂያ በመጻፍ ግንባታ አቁመው የነበሩ ስምንት ባለሀብቶች ግንባታቸውን እንዲያጠናቅቁ ማድረጋቸውንም አስታውቀዋል፡፡ በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ በማያጠናቅቁ ባለሀብቶች ላይ እርምጃ እንደሚወስዱም ተናግረዋል፡፡
በደብረ ታቦር ከተማ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው እየተነቃቃ መሆኑንም ኀላፊው አስታውቀዋል፡፡ በከተማዋ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለመሠማራት የሚፈልጉ ባለሀብቶች ጥያቄ እያቀረቡ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ከተማ አስተዳደሩም ባለሀብቶች መዋለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ለማድረግ፣ ውጣ ውረድን ለማሳጠርና ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ