ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን የግድቡ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ገለጸ፡፡

161
ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን የግድቡ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 08/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነትና የሚዲያ ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም ተናግረዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ መረጃ
• በመጋቢት ወር ብቻ ከ388 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል፤
• በ2013 ዓ.ም 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዷል፤
• በዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ 1 ቢሊዮን 672 ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል፡፡
ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ የሚደረገው ድጋፍ በገንዘብ ብቻ ሳይሆን ለግድቡ ድርድር ስኬት በማኅበራዊ የትስስር ገጽ አዎንታዊ ሀሳብ በማጋራት፣ ፊርማ በማሰባሰብ፣ ሰልፍ በማድረግ፣ ምሁራን ጥናቶችን በማቅረብ ለተደራዳሪዎች አቅም እየሆኑ ነው ብለዋል፡፡
የኪነጥበብ ባለሞያዎች “8100 A” አጭር የጽሑፍ መልእክት ማስታወቂያ በመሥራት ለግድቡ ግንባታ ያደረጉት አስተዋጾኦ ከፍተኛ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡
በአጭር የጽሑፍ መልዕክት 97 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉንም ዳይሬክተሩ ነግረውናል፡፡
ግብጽ ግድቡ እንዳይጠናቀቅ በምትሸርበው ሴራ በመቆጨት የኢትዮጵያ ሕዝብ በወኔና በቁጭት የበለጠ በመነሳሳት ለግድቡ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለአብነትም በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ዜጎች ባሳለፍነው መጋቢት ወር ብቻ 30 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል ነው ያሉት፡፡ በአንድ ወር ውስጥ ከዲያስፖራው ይህንን ያህል ብር መሰብሰቡም ድጋፉ ከሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከውጭ ሀገራትም ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ከፍተኛ መሆኑን ማሳያ እንደሆነ አንስተዋል፡፡
የሕዳሴ ግድብ ዋንጫ በተዘዋወረባቸው ክልሎች ድጋፉ የጎላ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ በአሁን ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ እየተዘዋወረ እንደሆነ እና 2 ቢሊዮን ብር ቃል ተገብቶ አንድ ቢሊዮን ብር ርክክብ ተፈጽሟል ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል ሕዳሴ ግድብ በደለል እንዳይሞላ የተፈጥሮ ሀብት ሥራዎችን ከመሥራት በተጨማሪ ለግድቡ ስኬት ከፍተኛ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዳይሬክተሩ እንዳሉት አጠቃላይ ሕዝቡ የግድቡ ባለቤት በመሆን “የዓባይ ጉዳይ የእኔ ጉዳይ ነው” በማለት እየተንቀሳቀሰ ነው፤ ግድቡ አንድነቱ እንዲጠናከር አድርጎታል፡፡ የግድቡ ግንባታ እውን እንዲሆን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ዳይሬክተሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተሠራ የጎርጎራ ከተማ መዋቅራዊ ፕላን እየተገመገመ ነው።
Next articleለ300 ዜጎች የሥራ እድል የሚፈጥረው ብራስ ጋርመንት በቅርቡ ወደ ምርት ይገባል፡፡