በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተሠራ የጎርጎራ ከተማ መዋቅራዊ ፕላን እየተገመገመ ነው።

217
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተሠራ የጎርጎራ ከተማ መዋቅራዊ ፕላን እየተገመገመ ነው።
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 08/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በቅርቡ በገበታ ለሀገር የልማት ፕሮጄክት የታቀፈችው ጎርጎራ ከተማ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ መዋቅራዊ ፕላኗ ተዘጋጅቶ በጎንደር ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተደረገበት ነው። በፕሮግራሙ የቀድሞው የጎንደር ከተማ ከንቲባ ኢንጅነር ማስተዋል ስዩም፣ የቀድሞው የባህርዳር ከተማ ከንቲባ ዶክተር መሐሪ ታደሰ እና የተለያዩ የሀገር ሽማግሌዎችና የመንግሥት ተወካዮች ተገኝተውበታል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ቢኒያም ጨቅሉ ዩኒቨርሲቲው በጎርጎራ ከተማና አካባቢው ዘርፈ ብዙ የማኅበረሰብ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰው አሁንም ጎርጎራን በሚገባት ልክ ለማሳደግ እንደሚሠራ አንስተዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስራት አፀደ ወይን (ዶክተር) ለረጅም ዘመናት ተረስታ የነበረችው ጎርጎራ ከተማን ወደ ልማት ለመመለስ በሚደረገው ሀገራዊ ጥረት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሚገባ እገዛ እንደሚያደርግ ጠቅሰው የከተማዋን መዋቅራዊ ፕላን ለማዘጋጀት ዩኒቨርሲቲው በመንግሥት የተሰጠውን አደራ መወጣቱን አንስተዋል።
የከተማ መዋቅራዊ እቅድ ከኢኮኖሚያዊ ጉዳይ አንፃር ጽሑፍ ያቀረቡት የቀድሞው የባሕር ዳር ከተማ ከንቲባ ዶክተር መሐሪ ታደሰ ነገ የተሻለ ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚታይበት ከተማ ለመገንባት ሀሳቡ በፖሊሲ ደረጃ መታገዝ እንዳለበት ጠቅሰዋል።
ዶክተር መሐሪ የሀገር ውጭ የሥራ ልምዳቸውን እያጣቀሱ ባቀረቡት ጽሑፍ የሚፈለገው እድገት እንዲመጣ ማኅበረሰቡን ያሳተፈ የሰላም እና አስተማማኝ ደኅንነት የመገንባት ሥራ መሠራት እንዳለበት ጠቁመዋል። በመርሃ ግብሩ የማኅበረሰብ አቀፍ ተኮር ኢንቨስትመንት፣ የውጭ ሀገርና የሀገር ውስጥ ከተሞች ፕላን ልምድና የጎርጎራ ከተማ መዋቅራዊ እቅድ ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ነው።
ዘጋቢ፡- ፍፁምያለምብርሃን ገብሩ – ከጎንደር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ሁልጊዜም ቢሆን መተባበርና መደራጀት ድል የሚያቀዳጅ ሀዲድ ነው” ዶክተር አረጋዊ በርሄ
Next articleለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን የግድቡ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ገለጸ፡፡