“ሁልጊዜም ቢሆን መተባበርና መደራጀት ድል የሚያቀዳጅ ሀዲድ ነው” ዶክተር አረጋዊ በርሄ

268
“ሁልጊዜም ቢሆን መተባበርና መደራጀት ድል የሚያቀዳጅ ሀዲድ ነው” ዶክተር አረጋዊ በርሄ
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 08/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ሁሉም የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች በትብብር ጮቄን ለማልማት የጀመሩት እንቅስቃሴ ለሕዳሴ ግድቡ ዘላቂነት ወሳኝ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የምስራቅ አፍሪካ የውኃ ጋን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የደም ስር እየተባለ ይጠራል፤ የ273 ትናንሽ የዓባይ ገባር ምንጮችና የ59 ትላልቅ ወንዞች መፍለቂያ ነው፤ እንደየወቅቱ ተለዋዋጭ ቢሆንም ለዓባይ ወንዝ እስከ 10 በመቶ ገደማ የውኃ ድርሻ እንደሚያበረክት ይገለጻል፤በዓመት ከ 5 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ ውኃ እንደሚመነጭበትም ይነገራል፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መሠረታዊ ዋስትናም ነው፤ ከፍተኛ ቅዝቃዜ እና ማራኪ መልከዓምድር አለው – ጮቄ የማኅበረሰብ ጥብቅ ስፍራ፡፡
ከ2011 ዓ.ም ወዲህ የማኅበረሰብ ጥብቅ ስፍራ እንዲሆን በአማራ ክልል መንግሥት ውሳኔ የተሰጠበት ይህ ስፍራ የተለያዩ የዱር እንስሳት፣ አዕዋፋትና ሀገር በቀል እፅዋት መገኛም ነው፡፡ የጮቄ ተፋሰስ ለረጅም ዘመናት በቂ እንክብካቤ ባለማግኘቱ የውኃው መጠን እንዲቀንስ እያደረገ ይገኛል፡፡
በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ባልደረባና የጮቄ ተፋሰስ ልማት ዳይሬክቶሬት አስተባባሪ ሆነው ያገለገሉት አረጋ ሹመቴ (ዶክተር) እንዳሉት ደኑ እየተመነጠረ ተመናምኗል፤ በዚህም ከተራራው የሚገኘው የውኃ መጠን እየቀነሰ ነው፡፡ ቀደም ብሎ ይገኝ የነበረው የታቆረ ውኃ አሁን የለም፣ በተራራው አናት ይታይ የነበረ በረዶም እየጠፋ ነው፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች በአመዛኙ አርብቶአደሮች በመሆናቸው ጮቄ ተፋሰስን ለልቅ ግጦሽ አጋልጠውታል፤ ለአፈር መሸርሸርም ምክንያት ኾኗል፡፡ የእርሻ ማስፋፋትና የቤት ግንባታ ፍላጎት መኖሩንም አንስተዋል፡፡ ይህም የአካባቢውን ሥነ-ምህዳር በማራቆት በተለይ በሕዳሴ ግድቡ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡ የአካባቢውን ሥነ-ምህዳር ወደ ነበረበት መመለስ እንደሚያስፈልግ የመከሩት ዶክተር አረጋ ለዚህም የመንግሥትን፣ የምሁራንን እና የማኅበረሰቡን ትኩረት እንደሚሻ አስገንዝበዋል፡፡
ዶክተር አረጋ እንዳሉት ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ አደረጃጀት በማቋቋም ተፋሰሱን ለማልማት ሲሠራ ቆይቷል፤ ይሁን እንጂ የሚፈለገው ውጤት አልተገኘም፡፡ በቅርቡ ሁሉም የኢትዮጵያ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ጮቄ ተፋሰስን ለማልማት ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ ስምምነቱ ጮቄ እንዲያገግም በማድረግ የሚያመነጨውን የውኃ መጠን በማሳደግ የግድቡን ዋስትና ዘላቂ ለማድረግ ያለመ ነው ብለዋል፡፡
ወደ ግድቡ የሚገባን ደለል በማስቀረትም የቆይታ ጊዜውን ያራዝማል፤ የቱሪዝም ገቢን ማሳደግ እንደሚያስችልም ነው ዶክተር አረጋ ያስታወቁት፡፡ ለዚህም ጥምረቱ ተጨባጭ ለውጥ ያመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡
ዶክተር አረጋ እንዳሉት ጮቄ በተለይም የተራራው ጫፍ እንዲያገግም ከንክኪ ነጻ ማድረግ ብቻ በቂ ነው፡፡ ለዚህም ማኅበረሰቡን ማስገንዘብና በጥናት ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ አማራጮችን መቃኘት ከጥምረቱ ይጠበቃል፡፡ መንግሥትም ከማኅበረሰቡ ጋር በመወያየት ችግሩን መፍታት ይኖርበታል፤ ካልሆነም በሕግ አግባብ የማስከበር ግዴታ አለበት ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል የአካባቢ፣ ደንና የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣንም ጮቄን በዘላቂነት ለማልማት እየሠራ እንደሆነ ገልጿል፡፡ በባለስልጣኑ የዱር እንስሳት ጥናትና ጥበቃ ዳይሬክተር አብርሃም ማርዬ እንዳሉት ለጥብቅ ስፍራው ጽሕፈት ቤት በማቋቋም የሰው ኀይል እየተሟላ ነው፡፡
ጮቄን በሚያዋስኑ 22 ቀበሌዎች ስካውት ለመቅጠርም እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ የተቋቋመው ጽሕፈት ቤትም ከምርምር ማዕከላትና ከኅብረተሰቡ ጋር በመሥራት ችግሮችን የመፍታት ኀላፊነት ተጥሎበታል፡፡ ለጊዜው 6 ሺህ 24 ሄክታር ለማልማት ቢታቀድም ዕቅዱን በስኬት ማጠናቀቅ ከተቻለ በሂደት ተጨማሪ ቦታ ለማልማት በትኩረት ይሠራል ብለዋል፡፡ ለዚህም ከምሁራን ጥምረቱ ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር ውጤታማ ሥራ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
“ሁልጊዜም ቢሆን መተባበርና መደራጀት ድል የሚያቀዳጅ ሀዲድ ነው” ያሉት ደግሞ የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተሩ አረጋዊ በርሄ (ዶክተር ) ናቸው፡፡ ለዚህም “ዓድዋን በዓይነ ኅሊና መለስ ብሎ መመልከት በቂ ነው” ብለዋል፡፡
ምሁራን በተናጠል የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ቢያበረክቱም ግብጽ ከሄደችበት ርቀት አንጻር ግን አናሳ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ዓባይን በብቸኝነት የመጠቀም “ብኩን ሕልም” ያላት ግብጽ ዕውነት ባይኖራትም በዓለምአቀፍ የዲፕሎማሲ መድረኮች የበላይነት መያዟንም በማሳያነት አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዓባይ በውኃ ተቋም ግንባታ ዘርፉ እምብዛም ያልሠራች መሆኑን በማንሳትም በደብረማርቆስ ዪኒቨርሲቲ አስተባባሪነት ጮቄን ለማልማት የተጀመረው እንቅስቃሴ ጥሩ ጅምር መሆኑን አንስተዋል፡፡
ዶክተር አረጋዊ እንዳሉት ጮቄን የማልማት እንቅስቃሴ የሀገሪቱን ውኃ የማመንጨት አቅም ያሳድጋል፣ ሕዳሴ ግድቡን ከደለል ይታደጋል፣ የተፋሰሱን ሀገራት ስጋትም ይመልሳል፡፡ ይህም “ኢትዮጵያ ባላት ጸጋ የመልማት እንጂ ማንንም የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላት ሁነኛ ማሳያ ነው” ብለዋል፡፡
ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተባበረ እና በተደራጀ መልኩ ለሕዳሴ ግድቡ የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ግድቡ ከሚሰጠው የቀጥታ ጥቅም ባለፈ የሀገር ቅርስም ነው” የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች።
Next articleበጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተሠራ የጎርጎራ ከተማ መዋቅራዊ ፕላን እየተገመገመ ነው።