
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሕብረት ማዕቀፍ ስር የሚደረገው የሦስቱ ሀገራት ድርድር እንዲቀጥል ጽኑ ፍላጎት እንዳላት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 08/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአውሮፓ ሀገራት ከሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ጋር በትብብር የግድቡን የድርድር ሂደት አስመልክቶ የኢትዮጵያን አቋም ግልፅ ለማድረግ፣ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እና የግድቡን ወቅታዊ ሁኔታ ለማስረዳት ያለመ ውይይት በበይነ መረብ ተካሂዷል።
ኢትዮጵያ በዓባይ ውሃ አጠቃቀም ዙሪያ በሦስቱ ሀገሮች ተቀባይነት ያለው ስምምነት ላይ ለመድረስ በአፍሪካ ሕብረት ማእቀፍ ስር የሚደረገው ድርድር እንዲቀጥል ጽኑ ፍላጎት እንዳላት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ተናግረዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ ሦስቱ ሀገራት የዓባይን ውሃ አጠቃቀም በተመለከተ ያላቸው ብቸኛ አማራጭ በትብብር እና በአፍሪካዊ ወንድማማችነት ስሜት በጋራ መሥራት ነው ብለዋል፡፡
ሁለተኛ ዙር ውኃ ሙሌት አስመልክተው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ኢትዮጵያ ለሱዳን እና ግብጽ የመረጃ ልውውጥ ለማድረግ በቅን ልቦና ተነሳሽነቱን በመውሰድ ተወካዮችን እንዲልኩ ጠይቃለችም ነው ያሉት፡፡
ሁሉም የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት አፍሪካዊ ሆነው ሳለ ጉዳዩን ለፖለቲካ ጠቀሜታ ሲባል የሚያራምዱት አቋም ተቀባይነት የለውም ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። ኢትዮጵያ በፍትሐዊ የውኃ አጠቃቀም ጽኑ እምነት ስላላት ማንንም የመጉዳት ዓላማ የላትምም ብለዋል፡፡
የቅኝ ግዛት ዘመን ውሎችን መልሰው በማምጣት የመጠቀም ፍላጎት ተቀባይነት የለውም ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ ባለፉት ሦስት ዓመታት የተደረጉት የሦስትዮሽ ድርድሮች የውኃ አሞላል ሂደቱ ሳይንሳዊ እና በመረጃ የተደገፈ መሆኑን ለማስገንዘብ በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል ብለዋል፡፡
የግብጽ እና ሱዳን ዓላማ ግድቡ ሳይሆን ከግድቡ ባሻገር ባለ የውኃ አጠቃቀም ላይ ያለመ ነው ያሉት ደግሞ በሕዳሴ ግድቡ ዙሪያ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ፕሮፌሰር ይልማ ናቸው። ሀገራቱ በ1959 (እ.አ.አ) የተደረሰውን የቅኝ ግዛት ዘመን ውል ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር ይፈልጋሉ ብለዋል ፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ እስከ አሁን ድረስ የዓባይ ውኃ አጠቃቀምን አስመልክቶ ምንም አይነት ስምምነት አለመኖሩን የጠቀሱት የሕግ ባለሙያ እና የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ለምለም ፍስሃ ኢትዮጵያ የውኃውን ፍትሐዊ ክፍፍል አጀንዳ አድርጋ ለትብብር ስትል ረጅም የድርድር መንገድ መጓዟ የሚያስመሰግን ነው ብለዋል።
በውይይቱ በአውሮፓ ሀገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች፣ በህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያን የወከሉ ዋና ተደራዳሪዎች፣ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን፣ ዓለም አቀፍ የውኃ ሕግ ባለሙያዎች፣ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ተገኝተዋል፡፡
ምንጭ:- በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ