
“በከተሞች የሚተገበሩ ሥራዎች ከዕቅድ ጀምሮ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ሊኖርበት ይገባል” የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 07/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የከተሞች ዕድገትና የኅብረተሰቡን ተሳትፎ በተመለከተ በሀገሪቱ የተሻለ ተሞክሮ ካላቸው ከተሞችና ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በባሕር ዳር ውይይት አድርጓል። በውይይቱ የተሳተፈችው ወጣት ሙሉነሽ ባይነሳኝ ጸጥታን ከማስከበር ጀምሮ በከተሞች እድገት ወጣቶች በንቃት ሊሳተፉ ይገባል ብላለች። ወጣቱ የሚገነቡ መሠረተ ልማቶችን መጠበቅና አካባቢውን ማጽዳት ይጠበቅበታል ነው ያለችው።
ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የቦንኬ ወረዳ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ማንዶሴ ሞኔ ባሕር ዳርን የምናውቃት በስም ብቻ ነበር ዛሬ ግን በአካል በመገኘታችን በርካታ ተሞክሮዎችን ለመቅሰም ችለናል ብለዋል። በውይይቱ የተለያዩ ከተሞች ካቀረቡት ምክረ ሀሳብ ብዙ እንደተማሩም አቶ ማንዶሴ አስረድተዋል።
ከተሞች ለነዋሪዎች ምቹ ሁኔታን መፍጠር ይጠበቅባቸዋል ያሉት ደግሞ የሐረር ከተማ ሥራ አስኪያጅ በቀለ ተመሥገን ናቸው። “ሕዝብን ያላማከለ ሥራ ውጤት ላይ እንደማያደርስ ከባለፉት ተሞክሮዎቻችን አይተናል” ያሉት ሥራ አስኪያጁ ኅብረተሰቡ በሚሠራለት ሥራ ዳር ቆሞ ከማየት ወጥቶ በቀጥታ ሊሳተፍ ይገባል ብለዋል። እያንዳንዱ ሥራ ከማኅበረሰቡ የተወከለ ባለቤት ሊኖረው ይገባል ነው ያሉት። ከተማን የሚያስተዳድር መሪ የተለያዩ ተሞክሮዎችን መቅሰም እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዲኤታ መስፍን አሠፋ (ዶክተር) “ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ተውጣጥታችሁ ዛሬ ባሕር ዳር የተገኛችሁ የሥራ ኀላፊዎችና ባለድርሻ አካላት የውቢቷ ባሕር ዳርን ተሞክሮ ወስዳችሁ በመጣችሁበት አካባቢ ልትተገብሩ ይገባል” ብለዋል። የበለጸጉ ከተሞችን በሀገሪቱ ለማየት ኅብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ ሊያደርግ ይገባልም ብለዋል። “በከተሞች የሚፈጠሩ ችግሮችም ሆነ መልካም ነገሮች ገፈት ቀማሽ የሆነው ኅብረተሰብ ለሁሉም ተግባር መፍትሄ ነው” ብለዋል። የሚገነባ መሠረተ ልማት ዘላቂነቱ እንዲረጋገጥ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ መኖር አለበት ነው ያሉት ዶክተር መስፍን።
ባሕር ዳር ኅብረተሰቡን ያሳተፉ በርካታ ሥራዎች የተከናወኑባት ከተማ ናት ያሉት ዶክተር መስፍን ከተማዋ የአረንጓዴ አሻራ ሥራዎችን በመንከባከብ፣ ጽዱና ውብ በማድረግ፣ ፓርኮችን በመንከባከብና በማልማት ሥራዎች በርካታ ተሞክሮዎች እንዳሏትም ጠቅሰዋል።
“ባሕር ዳር ምርጥ ተሞክሮ ስላላት ነው መድረኩን በባሕር ዳር ለማካሄድ የወሰነውም” ብለዋል። ለከተሞች ሁለንተናዊ እድገት የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ ነው ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው የኅብረተሰቡ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሁሉ ሊቀረፉ የሚችሉት ኅብረተሰቡ ሲሳተፍበት ነው ብለዋል። ኅብረተሰቡም ከዕቅድ እስከ ክንዉን ድረስ ሊሳተፍ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት። “በሥራዎቻችን ኅብረተሰቡን ካላማከርን ፍላጎትና አቅርቦት ሊጣጣሙ አይችልም” ብለዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ