
በአሠራር እና በስርጭት መዛባት የመጣውን የኑሮ ውድነት ለመሻገር በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ የምጣኔ ሀብት ምሁር ተናገሩ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 07/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በአንድ ሀገር ጤናማ የሆነ የኢኮኖሚ ፍሰት እንዲኖር በብድርና በዕርዳታ ብቻ የቆመ ኢኮኖሚ ከመገንባት ይልቅ ሀገር በምታመነጨው ሀብት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራትና በዘመናዊ አሠራር መደገፍ እንደሚገባ የምጣኔ ሀብት ምሁርና ተመራማሪ አለማየሁ ከበደ (ዶክተር) ተናግረዋል፡፡ ሀገር እያመነጨች ያለውን ውስን ሀብት ያለአግባብ የሚጠቀሙ ወገኖች መበራከታቸውና ፍትሐዊ የምርት ሥርጭት አለመኖሩ ለችግሩ ምክንያት መሆኑን የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ይገልጻሉ፡፡
በኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት ዜጎችን ፈተና ውስጥ ጥሏል፡፡ የዋጋ ግሽበቱ ባላፉት ሦስት አስርት ዓመታት ገደማ ሲገፋና ሲደጋገፍ የመጣ ነው ያሉት የምጣኔ ሀብት ምሁሩ እና ተመራማሪው ዶክተር አለማየሁ በተለይ በምግብ ነክ እና በሸቀጥ ዓይነቶች ላይ የታየው የዋጋ ግሽበት ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ የመጣ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በሴፍቲኔት በኩል የነበረውን የውጭ እህል ድጋፍን በማስቀረት ጥሬ ገንዘቡን ወደ ገበያው እንዲለቀቅ መደረጉን ተከትሎ ብዙ ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚው እንዲገባ ተደርጓል፤ በዚህም ምክንያት ግሽበቱ መውጣት ጀምሯል፤ ይህም ለኢትዮጵያ አሁን ላይ ለደረሰው ጤናማ ያልሆነ ምጣኔ ሀብታዊ ጫና በዋና ምክንያትነት ይጠቀሳል ባይ ናቸው:: በኢትዮጵያ ካለፉት 17 ዓመታት ገደማ ጀምሮ የታየው ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት መሠረታዊ ለውጦችን ያሳየ እንደነበር አይካድም ያሉት ዶክተር አለማየሁ በዚያው ልክም ከኢትዮጵያ ሚሌኒየም በኋላ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት ተከስቷል፤ይህ ደግሞ በከተሞች የመኖሪያ ቤት፣ በምግብና አልባሳት ላይ ብቻ ሳይሆን እንደ ትራንስፖርት፣ ትምህርትና ማኅበራዊ አገልግሎቶች በመሳሰሉ መስኮች ላይም እየተፈጠረ የመጣው ምጣኔ ሀብታዊ ጫና ከብዙኃኑ ሕዝብ የዕለት ገቢ ጋር ያልተመጣጠነ መሆኑ ችግሩን የባሰ አድርጎታል ብለዋል፡፡
በአለፈው ዓመት የዓለም ብሎም የሀገሪቱ ፈተና የነበረው የኮሮናቫይረስ ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭን ያስከተለ መሆኑ፣ እንደ ሀገር ለደቀቀው ኢኮኖሚና የኑሮ ውድነት፣ በሰሜኑ በኩል ሕግ ለማስከበር በተወሰደው እርምጃ የወጣው ወጭ እና በሀገሪቱ የሚፈጠሩ አለመረጋጋቶች ለግሽበቱ መንስኤ ናቸው ብለዋል፡፡ አሁንም የገበያ መረጋጋቱ ጉዳይ ትኩረት እንደሚሻና አልሞ መንቀሳቀስ ከመንግሥት፣ ከንግዱ ማኅበረሰብና ከማኅበራት የሚጠበቅ ተግባር ነው ያሉት የምጣኔ ሀብት ምሁሩ እና ተመራማሪው የወቅቱ ትልቁ ፈተና በሀገሪቱ የወጡ የንግድና የገበያ ሕግጋትን አጥብቆ በመተግበርና በማስተግበር በኩል የፖለቲካ ተሿሚዎች ተግባር ነው ብለዋል፡፡
በአሠራር እና በስርጭት መዛባት የመጣውን የኑሮ ውድነት በእውቀት በመምራትና በቅንጂት በመሥራት መፍታት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ መንግሥት የሀገር ደኅንነትና ሰላምን ከመጠበቅና ከማስተዳደር ባሻገር በኢኮኖሚው መስክም ይሳተፋል፤ አቅጣጫ ያስቀምጣል፣ ዕቅድ ያወጣል ብለዋል፡፡ የነፃ ገበያው ኢኮኖሚ ውስጥ እውቀቱና ጉልበቱ ያላቸው ሁሉ ገብተው ሀገር እንዲጠቅሙ የማድረግ ሥራ መሠራት እንደሚገባውም ዶክተር አለማየሁ ጠቁመዋል፡፡
እውቀት በሀገሪቱ ዋጋ ተሰጥቶት ሀሳብ ያላቸውን ገንዘብ ካላቸው ጋር በማጣመር እና አሠራር በማበጀት ኢኮኖሚው ውስጥ ማስገባት ይገባል ብለዋል፡፡ የደላሎች ስግብግብነትና የኑሮ ውድነት ወቅታዊ የገበያ ፈተናዎች በመፍጠር ማኅበረሰባዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ጫና ፈጥሯል ነው ያሉት፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መለስ ቀለስ የሚለው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት፣ መንግሥት ሀገር በማረጋጋት ላይ በመጠመድና መሰል ወቅታዊ ፈተናዎች የራሳቸው አሉታዊ ተፅዕኖ በገበያው ላይ ማሳደራቸውን ዶክተር ዓለማየሁ ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ጋሻው ፈንታሁን – ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ