
በክልሉ ያለውን የመሠረተ ልማት ችግር ለማስተካከል በትኩረት እየሠራ መሆኑን የሱማሌ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን
ቢሮ አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 06/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት 20 ዓመታት የሱማሌ ክልል እንደ ሀገር የሚጋራቸው ችግሮች ቢኖሩም
በተለይ ደግሞ ክልሉ ያለውን ሀብትና እድል እንዳይጠቀም የሚደያርጉ ፈተናዎች ገጥመውት ቆይተዋል፡፡ የቀድሞው የሱማሌ
ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኀላፊ ዶክተር አብዱልፈታህ ሸህ-ቢሂ በክልል ያለውን መዋቅራዊ ችግር የለየው አዲሱ
አመራር ያለውን ክፍተት በቁርጠኝነትና በባለቤትነት ለመከወን አዲስ መዋቅር በመዘርጋት ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እየሠራ ነው
ብለዋል፡፡
ባለፉት 18 ወራት ብቻ በሱማሌ ክልል በመሠረተ ልማት በኩል የተሠራው ሥራ ከአሁን ቀደም ከተከናወነው የተሻለ መሆኑን
ጠቅሰዋል፡፡ በክልሉ ያለውን የመንገድ ስርጭት ችግር ለመፍታት የተከናወነው ተግባር ውጤታማ ነው ብለዋል፡፡
ቀደም ብሎ የክልሉን ከተሞች ከገጠር አነስተኛ ከተሞችና ቀበሌዎች የሚያገናኙ መንገዶች አልነበሩም፤ከሐረር-ጎዴ የሚደርስ
እና በፌዴራል መንግሥት የተሠራ የአስፋልት መንገድ ብቻ በክልሉ ነበረ ያሉት ዶክተር አብዱልፈታህ ይህን ለመቀየር የተሠራው
ሥራ የሚበረታታ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ከጅግጅጋ ከተማ ውጭ ከሀርረ -ጎዴ- ቶጎ ጫሌ-አይሻ መንገድ ባለፈ በከተማ ውስጥ ምንም አስፋልት አልነበራቸውም ያሉት
ዶክተር አብዱልፈታህ ልማቱን ተደራሽ ለማድረግ የመንገድ ተደራሽነትን የማሳደግ ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡
ክልሉ ያለው የኤሌክትሪክ ኀይል ተደራሽት እና የመሠረተ ልማት ዝርጋታም ዝቅተኛ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍም
ባለፉት 6 ወራት ብቻ ከ10 በላይ ከተሞችን የኤሌክትሪክ ኀይል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡ 30 የሚሆኑ የወረዳ
ከተሞችም በቀጣይ ወራት ውስጥ የቴሌኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ዝርጋታዎች እየተሠሩ እንደሆነ በተለይም
ለአሚኮ ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ አዲሱ አመራር ያደረገው የክትትል ውጤት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ያለውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍም በተለይ በክልሉ ካሉ 11 ዞኖች መካከል በ10ሩ ዞኖች ለጤና ባለሙዎች እና
ለመምህራን የመኖሪያ ቤቶችን በመገንባት ማስረከብ ተችሏል ብለዋል፡፡
የጅግጅጋ ከተማን የወደፊት የማስፋት እና የመልማት ጥያቄዋን ግምት ውስጥ ባስገባና ሳይንሳዊ መንገድን የተከተለ አዲስ
መዋቅራዊ ፕላን እየተሠራ መሆኑን ያወሱት ዶክተር አብዱልፈታህ ገላዴ፤ሜራብእሜ፤ ቆሬሌ፤ ዶሎባይ እና ሸጎሽ ከተሞችም
መዋቅራዊ ፕላን እየተዘጋጀላቸው ነው ብለዋል፡፡ እስካሁንም ከላፈው 2011 ዓ.ም ወዲህ 25 የሚደርሱ የክልሉ ከተሞች
ማስተር ፕላናቸው እንደተጠናቀቀ ተገልጿል፡፡
ዘጋቢ፡- ጋሻው ፈንታሁን
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m