
“እስካሁን በነበሩ የቅድመ ምርጫ ተግባራት የጸጥታ ችግር ፈታኝ ነበር” ምርጫ ቦርድ
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 06/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እስካሁን ያከናወናቸው ተግባራቱን ለፓርቲዎች ይፋ እያደረገ ነው። የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ በተገኙበት እየተካሄደ በሚገኘው ውይይት የፓለቲካ ፓርቲዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በውይይቱ የቅድመ ምርጫ ሂደቱ የእስካሁን ጉዞና በሂደቱ ያጋጠሙ ሁኔታዎች ትኩረት ተደርጎባቸዋል። በሪፖርቱ እስካሁን ተግባሩም ለመራጮች የምዝገባ ቁሳቁስ ስርጭት ማከናወኑን አሰረድቷል። ስርጭቱ በቦሌ ካርጎ፣ በኤግዚቢሽን ማዕከል እና በቦርዱ ሎጀስቲክስ ማእከል በመከፋፈል የድልደላ እና የስርጭት ሥራዎች ተሠርተዋል።
የድልድል ሥራው ላይ ከፍተኛ የጥራት ቁጥጥር ለማድረግ በማሰብ ገለልተኛ በሆነ ድርጅት የቁጥጥርና የድልድል ሥራዎች ጊዜውን ጠብቆ የመራጮች ምዝገባ የጊዜ ሰሌዳ አስቀድሞ መከናወኑ ተጠቅሷል፡፡
የመራጮች ምዝገባ የሰነድ ዝግጅት ድልድል እና ስርጭት የሎጅስቲክስ ብዛት እና ስፋት ያለው መሆኑን የጠቀሰው ቦርዱ በሀገሪቱ የተሽከርካሪ መሰረተ ልማት አንጻር የመንገዶች በቂ ደረጃ ላይ ያለመሆን እና መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ አስቸጋሪ መሆን ተግዳሮቶች ነበሩ ብሏል።
ከተፈናቃዮችና ፀጥታ ጉዳይ ጋር በተያያዘም የመራጮች ምዝገባ እና በፀጥታ ስጋት እና የመረጃ መዘግየት የተነሳ የመራጮች ምዝገባ ቁሳቁሶች ስርጭት የዘገየባቸው ክልሎች
1. ኦሮሚያ ክልል – ምእራብ ወለጋ፣ ምስራቅ ወለጋ፣ ሆሮጉድሩ እና ቄለም ወለጋ (ክልሉ ስለቀበሌዎቹ ፀጥታ የሰጠው መረጃ ዘግይቶ የደረሰ መሆኑ መረጃዎቹም ከደረሱ በኋላ መጣራት ስለነበረባቸው የዘገየ)
2. ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን እና ከማሺ ዞን (በከፊል)
3. አማራ ክልል- ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር እና ሰሜን ሸዋ (ጨፋ ሮቢት፣ ሸዋሮቢት ማጀቴ፣ አጣየ፣ አርጎባ ልዩ ወረዳ) ፣ ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር (ከትግራይ ክልል ጋር የሚዋሰኑ 27 የምርጫ ጣቢያዎች)
4. ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል – ጉራፈርዳ በአራት ቀበሌዎች፣ ሱርማ፣ ዘልማም (ግጭቶችን ተከትሎ የምርጫ ተግባር መቀጠል መቻሉን የሚገልጽ መረጃ አለመኖር) ይጠቀሳሉ፡፡
“እስካሁን በነበሩ የቅድመ ምርጫ ተግባራት የጸጥታ ችግር ፈታኝ ነበር” ብሏል ቦርዱ፡፡
በጸጥታ ችግር የተነሳ በ4 ሺህ 126 የምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደባቸው አለመሆኑንም ገልጿል።
እስካሁን ባለው ተግባር የመራጮች ምዝገባ ውጤታማ ባለመሆኑ በቀጣይ
1. የአጭር የስልክ ጽሑፍ መልእከት ለ35 ሚልዮን ዜጎች ተደራሽ ይደረጋል፤
2. የተፈናቀሉ ዜጎች እና ተደራሽነታቸው ዝቅተኛ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን የሚያስተምሩ ዘጠኝ የሲቪል ማኅበራት በቦርዱ ልዩ ድጋፍ ይሰጣል
3. ቀጣይ የመራጮች ምዝገባ መልእክቶች ( በአምስት ቋንቋዎች)
4. ከ40 በላይ ቋንቋዎች የማስተርጎም ተግባር እና የመራጮች ምዝገባ መረጃ ይካሄዳል
5. የፓለቲካ ፓርቲዎች እና መገናኛ ብዙኃን የመራጮች ምዝገባ ዘመቻን እንዲያግዙ ይደረጋል ተብሏል፡፡
ዘጋቢ፡- እንዳልካቸው አባቡ – ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ