ዩጋንዳ እና ሩዋንዳ በወሳኝ ጉዳዮቻቸው ላይ በኪጋሊ እየመከሩ ነው፡፡

217

ባሕር ዳር፡ መስከረም 6/2012 ዓ.ም (አብመድ) የሀገራቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት በኪጋሊ እያካሄዱት ያለው ውይይት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ማጠናከርን ዓላማ ያደረገ ነው፡፡

የዩጋንዳ ልዑክ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳም ኩተሳ የተመራ ነው፡፡ አንጎላና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ደግሞ ሁለቱ ጎረቤት ሀገራት ስምምነት ላይ እንዲደርሱ በአደራዳሪነት ድርሻቸውን እየተወጡ ነው፡፡

የዩጋንዳና የሩዋንዳ ከፍተኛ ባለስልጣናት በውይይታቸው ባለፈው ነሐሴ አንጎላ ላይ ተፈራርመውት በነበረው የመግባቢያ ሰነድ ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ተነግሯል፡፡ ባለስልጣናቱ በሀገራቱ አዋሳኝ ቦታዎች ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲኖር፣ ነጻ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲሰፍንና የፖለቲካ ሁኔታው እንዲሻሻል እንደሚሰሩም ይጠበቃል፡፡

ያለፈው ነሐሴ ስምምነታቸው በዋናነት በሀገራቱ ጸጥታ እና የዜጎቻቸው ኑሮ መሻሻል ላይ ተኮረ ነበር፡፡ በወቅቱም ሁለቱ ሀገራት ነጻ የድንበር አካባቢ የሰዎች እንቅስቃሴ እና ንግድ እንዲካሄድ እንዲሆም የሁለቱን ሀገራት ዜጎች ህይዎት ለማሻሻል ተስማምተው ነበር፡፡

የፖልካጋሜ መንግስትን የሚቃወሙ ኃይሎችን ትደግፋለች በሚል ሩዋንዳ በዩጋንዳ ላይ ተደጋጋሚ ውንጀላዎችን እያቀረበች መሆኗ ይታወቃል፡፡ ዩጋንዳ ደግሞ ውንጀላው ከእውነት የራቀ ነው በማለት ስታስተባብል ቆይታለች፡፡ ይህን ተከትሎ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ሻክሮ ቆይቷል፡፡ ሁለቱን ሀገራት የሚያገናኙ የጋራ ድንበሮች በመዘጋታቸው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው እየተዳከመ እንደሆነም ነው የተዘገበው፡፡

ምንጭ፡- ሲ ጂ ቲ ኤን

ዘጋቢ፡- ሀይሉ ማሞ

Previous article“የሦስተኛ ወገን መድን ዋስትና ካልለጠፍን ስምሪት አይሰጠንም፡፡” አሽከርካሪ
Next articleለጣና ሸልማት አሸናፊዎች ነፃ የትምህርት እድል እንደሚሰጥ ተገለጸ፡፡