
የሕዝብን ደኅንነት ለመጠበቅ ውስጣዊ አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 05/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ከሶስቱም የጎንደር ዞኖች ለተውጣጡ የጽጥታ አመራሮች፣የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በሰላም ግንባታ አስፈላጊነት ዙሪያ በጎንደር ከተማ ስልጠና እየተሰጠ ነው። ተሳታፊዎቹ ከሰሜን፣ ከምዕራብና ከማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች ከሚገኙ 11 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ናቸው።
በስልጠናው በሰላምና ደኀንነት ዙሪያ የሚሠሩ ከመንግሥትና ከሃይማኖት ተቋማት የተውጣጡ ግለሰቦችም ተገኝተዋል። የአማራ ክልል ሰላምና የሕዝብ ደኀንነት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ አቶ አወጣ ገብሩ ሁሉን አቀፍ የሰላም እሴቶችን እውን በማድረግ የሕዝብን ደኅንነት መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን አስታውቀዋል። ለዚህም ደግሞ ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ ውስጣዊ አንድነትን ለማጠናከር የሀገር ሽማግሌዎች፣የሃይማኖት አባቶችና የጸጥታ አካላት ቅንጅታዊ አሠራርን ማጎልበት እንደሚጠበቅባቸው ነው ያስረዱት።
የስልጠናው ተሳታፊዎችም ለእርቀ ሰላምና ለሰላም ግንባታዎች ቅድሚያ ሰጥተው ሊሠሩ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።
በምክክሩ የተገኙ የሃይማኖት አባቶችም ሃይማኖታዊ አስተምህሮቶቻቸው ለሰላም ቅድሚያ እንደሚሰጥ ጠቁመው ለሰላም ግንባታ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ስልጠናው የአማራ ክልል ሰላምና የሕዝብ ደኅንነት ቢሮ ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የባሕር ዳርና ደሴ ሰበካ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ነው፡፡ ስልጠናው ለሁለት ቀን እንደሚሰጥም ታውቋል።
ዘጋቢ፡- ሀይሉ ማሞ – ከጎንደር
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ