በአማራ ክልል የኮሮናቫይረስ መከላከያ ዘዴዎችን በአስገዳጅነት ለማስተግበር እየተሠራ መሆኑን ኢንስቲቲዩቱ አስታወቀ፡፡

120
በአማራ ክልል የኮሮናቫይረስ መከላከያ ዘዴዎችን በአስገዳጅነት ለማስተግበር እየተሠራ መሆኑን ኢንስቲቲዩቱ አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 05/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የኮሮናቫይረስን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና የሚያደርሰውን ተጽዕኖ ለመቀነስ የሦስት ወራት ዕቅድ መዘጋጀቱን የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት አስታውቋል፡፡
በኢንስቲትዩቱ የኀብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከል፣ መቆጣጠር፣ ምላሽ መስጠት እና መልሶ ማቋቋም ባለሙያ ተመስገን አንተዬ እንዳሉት በማኅበረሰቡ ዘንድ ኮሮናቫይረስን የመከላከል ተግባር ቀንሷል፤ በዚህም በቫይረሱ የመያዝ ምጣኔው በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል፡፡
የማኅበረሰቡ መዘናጋት ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለ መሆኑንም ነው ባለሙያው ያስታወቁት፡፡ በመሆኑም የቫይረሱን መከላከያ ዘዴዎች በአስገዳጅነት ለማስተግበር በክልሉ መንግሥት የሦስት ወራት ዕቅድ ተዘጋጅቷል፡፡
ዕቅዱ የተዘጋጀው የፌዴራል መንግሥት ባስቀመጠው አሠራር መሠረት የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡
የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የወጣው መመሪያ ቁጥር 30/2013 ይዘቱ ማንኛውም የማኅበረሰብ ክፍል የጥንቃቄ መልዕክቶችን እንዲተገብር የሚያደርግ ነው፡፡
አላስፈላጊ ስብሰባዎችን የሚከለክልና ሌሎች በርካታ ተግባራት ተካትተውበታል፡፡ እንደ አዲስ ያገረሸውን የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚከናወኑ ተግባራት እና በክልሉ የሚገኙ የጤና ተቋማት ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ተግባራቱን እንዴት መምራት እንዳለባቸውም ያስቀምጣል፡፡
ዕቅዱ ከጸደቀበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ተግባር ቢገባም የኮሮናቫይረስ መከላከልና መቆጣጠር ግብረኀይል ተወያይቶ ውሳኔ ስላላሳለፈበት በአስገዳጅነት ለመተግበር የሚያስችል የሕግ አግባብ አለመኖሩንም አንስተዋል፡፡ ለዚህም ግብረኀይሉ ተወያይቶ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ነው ያስወቁት፡፡ ውሳኔውን ተከትሎ በአስገዳጅነት ወደ ተግባር እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡
የፍትሕ አካሉና የጸጥታ አካሉ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሚደርሰውን ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ኪሳራ ለማስቀረት ዕቅዱን ማስተግበር እንደሚጠበቅባቸውም አቶ ተመስገን አስታውቀዋል፡፡
ማኅበረሰቡም በጉዳዩ ላይ የሚስተዋልበት መዘናጋት ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለ መሆኑን በመረዳት ቫይረሱን ለመከላከል የወጡ የጥንቃቄ ርምጃዎችን በተገቢው መንገድ እንዲተገብር አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየኮሮናቫይረስን ለመከላከል ሳይቃጠል በቅጠል የሚለውን ብሂል እየተገበሩ እንደሆነ የባሕርዳር ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
Next articleየሕዝብን ደኅንነት ለመጠበቅ ውስጣዊ አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ፡፡