
“የሦስተኛ ወገን መድን ዋስትና ካልለጠፍን ስምሪት አይሰጠንም፡፡” አሽከርካሪ
“በኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተሽከርካሪዎች ቢኖሩም ሦስተኛ ወገን መድን ዋስትና ያላቸው ከ 5 መቶ ሺህ አይበልጥም፡፡” በአማራ ክልል የመድን ፈንድ አስተዳድር ኤጀንሲ
“በተሽከርካሪ ከተገጩ በኋላ የአካል እንቅስቃሴ አልነበራቸውም፡፡ ለሦስት ቀናት በፈለገ ህይወት ሪፈራል ሆስፒታል የነፃ ህክምና እርዳታ ሲደረግላቸው ከቆዩ በኋላ አርፈዋል፡፡” ይህ አባታቸውን በመኪና አደጋ ያጡት የወይዘሮ ሙሉጎጃም በላይ ሀሳብ ነው፡፡
ነሐሴ 21 2010 ዓ.ም ነበር አባታቸውን በመኪና አደጋ ምክንያት ያጡት፡፡ የአቶ በላይ እጅጉ ሴት ልጅ ሙሉጎጃም አደጋው ከተከሰተ ከስድስት ወራት በኋላ ወደ መድን ፈንድ አስተዳድር ኤጀንሲ በመሄድ እርዳታ ጠየቁ፡፡ የአባታቸውን ህይዎት ባይመልስም ከኤጀንሲው ከ18 ሺህ 9መቶ ብር በላይ ካሳ እንደተሰጣቸው ነግረውናል፡፡ ኤጀንሲው ካሳ እንደሚከፍል ግንዛቤ ያልነበራቸው ወሮ. ሙሉጎጃም አሁን ስለሦስተኛ ወገን የተሽከርካሪ አደጋ ያወቁትን ለሌሎች በማሳወቅ ላይ ይገኛሉ፡፡
የሦስተኛ ወገን መድን ዋስትና ተጠቃሚ አሽከርካሪዎችን ለመቃኘት ወደ ባሕር ዳር አውቶብስ መናኸሪያ ሄደን ነበር፡፡ የሕዝብ ሁለት አሽከርካሪው ሳሙኤል ገነቱ ፅኑ ሶስተኛ ወገን መድን ዋስትና የሚያመላክተውን ማረጋገጫ ወረቀት ከተሽከርካሪው ፊት ለፊት መስታዎት ላይ ለጥፎ ተመለከትን፡፡ የሦስተኛ ወገን መድን ዋስትና ካልለጠፉ ስምሪት እንደማይሰጣቸው፤ በዓመት አንድ ጊዜም እንደሚያሳድስ አሽከርካሪው ነግሮናል፡፡
ዓመታዊ የተሽከርካሪ ፍተሻ (ቦሎ) እና ደረጃ ለመቀበልም የፀና ሦስተኛ ወገን መድን ዋስትና እንደ አንድ መስፈርት እንደሚጠየቅ ነው የተናገረው፡፡ አሠራሩ በጥንቃቄ ለማሽከርከር እንደሚያስችልም ነው አስተያዬት የሰጠው፡፡ በአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ የጤና ክብካቤ፣ ሀብት ማግኛና ጤና መድን መኮንን ወይዘሮ ህይወት ጥላሁን “ብስክሌትና ጋሪን ሳያጠቃልል በሞተር ኃይል በሚንቀሳቀስ ተሽከርካሪ አማካኝነት ማንኛውም ሰው ላይ ጉዳት ከደረሰ በማንኛውም ጤና ተቋም ህክምና ያገኛል፤ ከሁለት ሺህ ብር በላይ የሚያስፈልገው ህክምና ከሆነ ግን ጉዳቱን ያደረሰው አካል ገንዘብ ከፍሎ እዲያሳክም ወይም ተጎጂው በራሱ ወጪ እንዲታከም ይደረጋል” ብለዋል፡፡
በጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና በመድን ፈንድ አስተዳድር ኤጀንሲ የተዘጋጀውን ቅፅ በመሙላት ጤና ተቋማቱ ለተጎጂዎች እርዳታ ያወጡት ወጪ ታስቦ ሂሳባቸው እንደሚከፈላቸውም ነው አሰራሩ ላይ የተቀመጠው፡፡ በጤና ጥበቃ ቢሮው የጤና ተቋመት ይህን አገልግሎት እንዲጠቀሙ የሚደረገው ክትትል አናሳ እንደሆነና እንደተጨማሪ ሥራ በመውሰድ እንደሚንቀሳቀሱ ነው ወሮ. ህይዎት የጠቆሙት፡፡ በመሆኑም በክልሉ በሚገኙት 850 ጤና ጣቢያዎችና 82 ሆስፒታሎች ተደራሽ ለማድረግ አስቸጋሪ እንደሆነ ነው ያስረዱት፡፡ ያም ሆኖ እንደ ፈለገ ህይወት ሪፈራል ሆስፒታል ያሉ በጣም ጥቂት ሆስፒታሎች አገልግሎቱን እየሰጡ ነው፡፡ በቅርቡም ሁሉም ሆስፒታሎች አዋጁና መመሪያውን እንዲያውቁ በማድረግ ያለምንም ክፍያ አገልግሎቱን እንዲሰጡ ለማድረግ ስራ እንደተጀመረ ነው የተገለጸው፡፡
አብመድ ባደረገው ቅኝት የባሕር ዳር ጤና ጣቢያ አገልግሎቱን እንደሚሰጥ አረጋግጧል፡፡ የጤና ጣቢያው ኃላፊ አዳነ ሞገስ የመኪና አደጋ ሲደርስ እስከ 2 ሺህ ብር በሚደርስ ወጪ ተጎጂዎች እንደሚታከሙ መረጃው እንዳላቸው ነግረውናል፡፡ በተጠናከረ ሁኔታ አገልግሎቱን ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውንም ነው የነገሩን፡፡ ስለጉዳዩም መንገድና ትራንስፖርት፣ ፖሊስ ኮሚሽን፣ መድን ፈንድ አስተዳድር ኤጀንሲ እና የጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊዎች ምክክር አድርገዋል ብለዋል ወሮ. ህይዎት፡፡ በቀጣይ በተዋረድ የሚከታተል ባለሙያ ተመድቦለት ሥራው በበላይነት እንዲሰራ መግባባት ላይ መደረሱንም ነው ያስረዱት፡፡ በአማራ ክልል የመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ አዝመራው በቀለ አዋጅ 799/2005 ወጥቶ ከፀደቀ በኋላ የፈንድ አቅም ወደ መገንባት እንደተገባ ጠቁመዋል፡፡ የተሽከርካሪ ባለቤቶች የአነስተኛ አረቦን (ፕሪሚየም) እንዲከፍሉ ይደረጋል፡፡ በዚህ መሠረት የፀና የሦስተኛ ወገን መድን ዋስትና ይኖራቸዋል፡፡ በአማራ ክልል ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ለተጎጂዎች አገልግሎት ላይ ውሏል፡፡ በ2011 የበጀት ዓመት ደግሞ ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎ ለጤና ተቋማት ተሰጥቷል፡፡ በአዲሱ የበጀት ዓመትም 5 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ለክልሉ ተመድቧል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ወደ 1 ሚሊዮን የሚጠጋ ተሽከርካሪ ቢኖርም በቁጥጥር መላላት የተነሳ የፀና የሦስተኛ ወገን መድን ዋስትና ያለው ከ5 መቶ ሺህ እንደማይበልጥ አቶ አዝመራው ይናገራሉ፡፡ በመሆኑም ወደ አሠራሩ ያልገቡ አካላት እንዲገቡ፣ እድሳት ያላደረጉ እንዲያድሱ እየተሰራ ነው፡፡ አዋጁ ላይ እንደተቀመጠው ማንኛውም ተሽከርካሪ የሦስተኛ ወገን መድን ዋስትና ሳይኖረው ሲያሽከረከር ከተገኘ ከ3 ሺህ እስከ 5 ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ ቅጣት ወይም ከ 1 እስከ 2 ዓመት በሚደርስ እስራት ይቀጣል፡፡
ዘጋቢ፡- ኪሩቤል ተሾመ