የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ሳይቃጠል በቅጠል የሚለውን ብሂል እየተገበሩ እንደሆነ የባሕርዳር ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

154
የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ሳይቃጠል በቅጠል የሚለውን ብሂል እየተገበሩ እንደሆነ የባሕርዳር ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 05/2013 ዓ.ም (አሚኮ)
በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ከጊዜ ወደጊዜ እየተስፋፋ ነው፤ በፅኑ ህክምና ክፍል የሚገቡ የሕሙማን ቁጥርም እየጨመረና ገዳይነቱም እያደገ መምጣቱ አሳሳቢ ሆኗል፡፡
ወረርሽኙ እየከፋ ቢመጣም ኅብረተሰቡ ግን ጆሮ ዳባ ልበስ ያለው ይመስላል፤ ከሰሞኑ አሚኮ በተለይ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል መጠቀምን በተመለከተ በባሕር ዳር ከተማ ተዟዙሮ ነዋሪዎችን አነጋግሯል።
የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ በላይ አብዲሳ ወረርሽኙ ወደ ሀገር ውስጥ ከገባ ጀምሮ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንደሚጠቀሙ ነግረውናል።
“ብዙ ወጪ ሳይወጣ በቀላሉ በሽታውን መከላከል ከተቻለ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል መጠቀም ለምን ይከብደናል?” ሲሉ የሚጠይቁት አቶ በላይ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል መጠቀም ከጀመሩ ወዲህ ጉንፋንን ጨምሮ በትንፋሽ የሚተላለፉ በሽታዎችን በቀላሉ መከላከል መቻላቸውን አስረድተዋል።
ብዙን ጊዜ ማኅበረሰቡ ችግር ሲደርስበት እንጂ ቀድሞ የመጠንቀቅ ልምድ የለውም ያሉት ነዋሪው በየቦታው ሲዘዋወሩ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል የሚጠቀሙ ሰዎች ውስን ሆነው በማየታቸው እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል።
አምሳለቃ ንጉሤ ዳኘው በባሕር ዳር ከተማ የግሽዓባይ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፤ ሁልጊዜ የአፍና የአፍንጫ ጭምብል የሚጠቀሙት ራሳቸውን ጨምሮ ሌሎችንም ከበሽታ ለመጠበቅና ለማስተማር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
“በቅርቡ የዕድር አባላት ለስብሰባ ሲመጡ የአፍና የአፍንጫ ጭምብል ለብሰው እንዲመጡ ትዕዛዝ ተላልፎ ነበር፤ የሚያሳዝነው ነገር 10 ሰው ብቻ ነበሩ ትዕዛዙን ያከበሩት” ብለዋል አምሳለቃ ንጉሤ ፡፡
በየቀኑ ስለወረርሽኙ ትምህርት ቢሰጥም አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል ትምህርቱን ተግባራዊ እያደረገ አይደለም ይላሉ፡፡
የመንግሥትና የግል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የአፍና የአፍንጫ ጭምብል የማይጠቀሙ ሰዎችን አገልግሎት እንዳያገኙ ቢያደርጉ በሂደት ሁሉም ሰው ትዕዛዙን እንደሚተገብር ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ቴዎድሮስ አለኸኝ ሰው በሚበዛበት አካባቢ አዘውትረው የአፍና የአፍንጫ ጭምብል እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል፡፡ ወረርሽኙን ለመከላከል ሕግ አውጭው አካል ሕጉ እንዲተገበር የሚያደርገው ጥረት በጣም ደካማ ነው፤ የወጣውን አዋጅ ማክበርም ሆነ ማስከበር የሁሉም ዜጋ ኀላፊነት መሆን አለበትም ብለዋል፡፡
ወይዘሮ ይካኑ ሳልሌ የተባሉ ሌላዋ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ደግሞ ድንገት ከቤታቸው ስለወጡ የአፍና የአፍንጫ ጭምብል እንዳለበሱ ተናግረዋል፡፡ ተግባሩ ትክክል እንዳልሆነ የተናገሩት ወይዘሮዋ ቫይረሱ በድንገት ሊይዛቸው ስለሚችል የሰሩትን ስህተት እንደሚያርሙ ነግረውናል፡፡ “በሽታው በተለይ እድሜያቸው የገፋ ሰዎችን ስለሚያጠቃ በእንደኔ አይነት ዕድሜ ክልል የሚገኝ ሰው ከሌላው የበለጠ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅበታል” ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፍተኛ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በተገኙበት የድምፅ መስጫ ወረቀት የዕጩዎች አደራደር ቅደም ተከተል መወሠኛ ሎተሪ አካሄደ፡፡
Next articleበአማራ ክልል የኮሮናቫይረስ መከላከያ ዘዴዎችን በአስገዳጅነት ለማስተግበር እየተሠራ መሆኑን ኢንስቲቲዩቱ አስታወቀ፡፡