
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፍተኛ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በተገኙበት የድምፅ መስጫ ወረቀት የዕጩዎች አደራደር ቅደም ተከተል መወሠኛ ሎተሪ አካሄደ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 05/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መጋቢት 02/2013 ዓ.ም ከፍተኛ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በተገኙበት የድምፅ መስጫ ወረቀት የዕጩዎች አደራደር ቅደም ተከተል መወሠኛ ሎተሪ ብዙኃን መገናኛ ድርጅቶች በተገኙበት በልዩ ሁኔታ አካሂዷል።
የቦርዱ አመራሮች በተገኙበት የተካሄደውን የሎተሪ ሥነ-ሥርዓት በንግግር የከፈቱት የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ የሎተሪ ሥነ-ሥርዓቱ እንደ አንድ ፍትሐዊ አሠራር እንደሚቆጥሩት ተናግረዋል። የቦርዱ ተቋማዊ ለውጥ በተለያዩ ተግባራት እየተገለጸ አሁን ላይ መደረሱን የገለጹት ሰብሳቢዋ የተካሄደውን የድምፅ መስጫ ወረቀት የዕጩዎች አደራደር ቅደም ተከተል መወሠኛ ሎተሪም የዚህ አካል ነው ብለዋል።
ቀደም ሲል የገዥው ፓርቲ ዕጩዎች በቅደም ተከተሉ መጀመሪያ ላይ እንዲሆኑ ማድረግ ተለምዷዊ አሠራር እንደነበረ ያስታወሱት የቦርዱ ዋና ሰብሳቢዋ ይህውም የተወሠኑ መራጮች በሚመርጡበት ጊዜ መጀመሪያ ያዩትን የመምረጥ ተፈጥሮዋዊ ዝንባሌያቸው ላይ የራሱ የሆነ ተጽዕኖ ከማሣረፍ አንጻር ፍትሕዊ ያልሆነ ውጤቶችን ስለሚያመጣ በዕጣ መወሠኑን ቦርዱ አማራጭ አድርጎ እነደወሰደው አብራርተዋል።
በ12 የተመረጡ ምርጫ ክልሎች የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲ ዕጩዎችና የግል ተወዳዳሪዎች የድምፅ መስጫ ወረቀት ላይ የሚኖራቸው አደራደር ቅደም ተከተል ተለይቶበት ቦርዱ ወዳበለፀገውና አንዴ ከመዘገቡበት ማሻሻያ ማድርግ እንዳይችል ተደርጎ በተሠራው ዲጂታል ሲስተም ውስጥ ለሁሉም ግልጽ በሆነ ሁኔታ እንዲገባ መደረጉንም ገልጸዋል።
ሥነ ሥርዓቱን ከተከታተሉት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች መካከል የነፃነትና ዕኩልነት ፓርቲ ሊቀ-መንብር አብዱልቃድር አደም (ዶክተር) የድምፅ መስጫ ወረቀት የዕጩዎች አደራደር ቅደም ተከተል መወሠኛ ሎተሪው በሀገሪቱ የምርጫ ታሪክ የመጀመሪያና የምርጫ ቦርዱንም ገለልትኛነት የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል፡፡
የአብን ፓርቲ የፖለቲካ ጉዳዮች ኀላፊ ክርስቲያን ታደለ በበኩላቸው በሥነ-ሥርዓቱ መደሰታቸውንና ምርጫ ቦርድ እስካሁን ባለው ሂደት ገለልተኛነቱን እያረጋገጠላቸው እንደመጣ ተናግረዋል።
የወላይታ ሕዝብ ፓርቲ ሊቀ-መንበር የሆኑት ተክሌ ቦረና ምርጫ ቦርዱ በሀገሪቱ የምርጫ ታሪክ ተከስቶ የማያውቅ ወረርሽኝ በተከሠተ ጊዜ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመመካከር ቦርዱ ኃላፊነት በተሞላው ሂደት እዚህ መድረሱን አድንቀዋል።
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ንቅናቄ ተወካይ የሆኑት አብዱናስር ሁሴን በበኩላችው ፓርቲያቸው ኢትዮጵያን ወደከፍታ ለመውሰድ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡
የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑት ጌታነህ ባልቻም በተለያዩ መድረኮች የቦርዱን የእስካሁን እንቅስቃሴ እያመሰገኑ እንደመጡ ገልጸው ለሎተሪ ሥርዓቱ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።
በተጨማሪም ፓለቲካ ፓርቲዎቹ አሁን በምርጫ ሂደቱ ውስጥ አለን የሚሉትን ስጋት፣ ያጋጠማቸውን ችግሮች እና በምርጫ ብቻ ለመፍታት ያላቸውን ቁርጠንነት ገልጸዋል።
የብልጽግና ፓርቲ እጩ የሆኑት የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደገዥ ፓርቲ ከሌሎች ጊዜዎች የተለየ ምርጫ ለማከናወን ዝግጅት እንዳለ ገልጸዋል። የእጣ መውጣት ሥነ ሥርአቱም እጩዎች በድምጽ መስጫ ወረቀቱ ላይ ፊርማቸውን አስፍረው መጠናቀቁንም ከቦርዱ ማህበራዊ ተስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ