
በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጸሙ ማንነትንና ሃይማኖትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን እንደሚያወግዝ የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አስገነዘበ።
ሙስሊሙ ኀብረተሰብ የረመዳን ፆምን በፍቅርና በመተጋገዝ እንዲያሳልፍም ምክር ቤቱ ጥሪ አቅርቧል።
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 05/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ሙስሊሙ ኀብረተሰብ የ1 ሺህ 442ኛው የረመዳን ፆም ለፈጣሪው በመገዛት፣ በፍቅር፣ በመረዳዳትና በመተጋገዝ ሊያሳልፈው እንደሚገባ የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ገልጿል::
የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ለአዲስ አበባ ከተማና ከኢትዮጵያ ውጪ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሕዝበ ሙስሊሙ ዛሬ የተጀመረውን የ1ሺህ 442ኛው የረመዳን ፆም በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል::
የምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ሼህ አሊ መሃመድ ሽፋ የረመዳን ፆምን መጀመርን አስመልክተው፤ ረመዳን ወር የእዝነት፣ የፍቅር የአብሮነት የተቀደሰ እንዲሆን ምኞታቸውን ገልፀዋል:: ችግረኞችን፣ አቅመ ደካሞችን እንዲሁም ወላጅ አልባ ህጻናትን በማገዝና ምጽዋት በመለገስ ሕዝበ ሙስሊሙ እንዲያሳልፍም ጥሪ አስተላልፈዋል::
ረመዳን የእዝነትና የራህመት ወር በመሆኑ በከተማው የሚገኘው ሙስሊሙ ሕብረተሰብ የረመዳን ወርን በኢባዳ፣ በፍቅር ፣ በመረዳዳት እና በመተጋገዝ ሊያሳልፈው እንደሚገባ አስገንዝበዋል::
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ የፅኑ ህሙማን ቁጥር ከዕለት ዕለት እየጨመረ መምጣቱን አስታውሰው፤ በዚህ በተቀደሰ ወር ውስጥ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ለፀሎት በሚሰባሰብበት ጊዜ የጤና ባለሙያዎች የሚያስተላልፏቸውን ምክሮች በመቀበልና በመተግበር አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉም አሳስበዋል::
በተለያዩ ክልሎች የሚታዩ ማንነትንና ኃይማኖትን መሰረት ባደረጉ ጥቃቶች፤ ለመፈናቀል፣ ለንብረት መውደም እንዲሁም ለህጻናት፣ ለእናቶችና አዛውንቶች ህይወት መቀጠፍ ምክንያት መሆኑን አስታውሰው፤ የእስልምና ሃይማኖት አስተምህሮትና የእምነቱ መሪዎች አጥብቀው እንደሚያወግዙም ተናግረዋል::
ኢትዮጵያውያን ድርጊቱን በማውገዝ ለህዝቡ መልካም በማሰብና ቅድሚያ በመስጠት ችግሩን በውይይት መፍታት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል::
የህዳሴ ግድብ ግንባታን አስመልክቶ ከውጭ ኃይሎች እየተቃጣ ያለውን ትንኮሳ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት በሀገራዊ መንፋስ በመቆም ሊያወግዙት ይገባል ብለዋል:: ለጋራ ሀብታቸው በመቆም ግንባታው እስከሚጠናቀቅ ድረስ በገንዘብና በተለያዩ ድጋፎች እገዛ ማድረጋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም መክረዋል::
ዘንድሮ ለሚካሄደው 6ኛው አገራዊ ምርጫ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚያደርጉት ቅስቀሳም ሰብዓዊ መብትን ባከበረ መልኩ በሰላማዊ መንገድ ሊከናወን ይገባል ብለዋል:: ሙስሊሙ ሕብረተሰብ የምርጫ ካርድ በመውሰድ መሪዎችን በመምረጥ ሀገራዊ ግዴታውን እንዲወጣም ጥሪ ማቅረባቸውን የዘገበው ኢፕድ ነው::
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ