
እድሜአቸው የገፉ እና ተጓዳኝ ህመም ያለባቸው ዜጎች የኮሮና ቫይረስ ክትባትን እንዲወስዱ ተጠየቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 05/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በሁሉም የመንግሥት የጤና ተቋማት ተደራሽ በመሆን ዕድሚያቸው ከ55 ዓመት በላይ ዕድሜ ክልል የሚገኙና ተጓዳኝ ሕመም ያለባቸው ዜጎች ክትባቱን እንደሚወስዱ ተገልጿል፡፡ ያም ሆኖ ለበርካታ ዜጎች መረጃ ባለመድረሱ በሚፈለገው ልክ ወደ ጤና ተቋማት በመቅረብ ክትባቱን ለመወሰድ ውስንነቶች እንዳሉ ከክልሉ ጤና ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
አቶ ወንዴ አያናው በሽምብጥ ጤና ጣቢያ ለተጓዳኝ ህክምና በመሄድ የኮሮና ክትባት የወሰዱ የ60 ዓመት አዛውንት ናቸው፡፡ አዛውንቱ እንደሚሉት መድኃኒቱን ከወሰዱ በኃላ በጤናቸው ላይ ምንም አይነት ችግር አላጋጠማቸውም፡፡
መንግሥትም ክትባቱ ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ የሚሆንበትን አሠራር በማመቻቸቱ ሰዎች ስለ ክትባቱ ሌላ አሉባልታዎችን ወደ ጎን ትተው መከተብ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የክትባት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ወርቅነህ ማሞ እንደገለጹት ዕድሜያቸው ከ55 ዓመት በላይ የሆኑና ተጓዳኝ ህመም ያለባቸው ዜጎች መድኃኒቱን እንዲወስዱ ለሁሉም የመንግሥት የጤና ተቋማት በቂ የክትባት መድኃኒት ተልኳል፡፡ ዜጎች ክትባቱን እንዲወስዱ መልዕክቱ በጤና ቢሮ በኩል መተላለፉንም አስርድተዋል፡፡
ባለሙያው ሰዎች በአቅራቢያቸው በሚገኘው ጤና ተቋም በመሄድ ክትባቱን መወሰድ እንደሚችሉም ተናግረዋል፡፡ በአማራ ክልል በጤናው ዘርፍ የሚገኙ ከ15ሺህ በላይ ባለሙያዎች ክትባት መውሰዳቸውን የገለጹት አቶ ወርቅነህ ዕድሜያቸው ከ55 በላይ የሆኑና ተጓዳኝ ህመም ያለባቸው ዜጎች በባሕር ዳር ከተማ መከተብ ጀምረዋል ነው ያሉት፡፡ ይህም ሆኖ በሁሉም አካባቢዎች መልዕክቱ ባለመድርሱ ክትባቱን መወሰድ የሚገባቸው ዜጎች ወደ ጤና ተቋማት በመቅረብ ክትባቱን እየወሰዱ ባለመሆኑ ባለሙያዎች ግንዛቤ መፍጠር አለባቸው ብለዋል፡፡
ዜጎችም የክትባቱ ተጠቃሚ በመሆን ወረርሽኙ ከሚያስከትለው ጉዳት ራሳቸውን መከላከል እንዳለባቸው መክረዋል፡፡ በመጀመሪያ ዙር የቀረበው መድኃኒት በጤናው ዘርፍ የሚሠሩ ባለሙያዎችን ታሳቢ ያደረገ ነው ያሉት አቶ ወርቅነህ በአሁኑ ወቅት ተጨማሪ ሰዎች እንዲከተቡ ተጨማሪ የክትባት መድኃኒት በአማራ ክልል በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች፣ ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች በሚገኙ ጤና ጣቢያዎች መላካቸውን ተናግረዋ፡፡
‹‹ክትባቱን መወሰድ ሌላ የጎንዮሽ ጉዳት ይኖረዋል›› ብለው የሚያስቡ ዜጎችም መድኃኒቱ በዓለም ጤና ድርጅትና በሀገር ውስጥ በሚገኙ ባለሙያዎች የተረጋገጠ በመሆኑ ያለምንም ፍርሃት መድኃኒቱን በመውሰድ ቫይረሱ ከሚያደርሰው ጥፋት ራሳቸውን መታደግ እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
ከጥንቃቄ ጉድለት ቫይረሱ በስፋት እየተስፋፋባቸው ያሉ ሀገራትም በፍጥንት ክትባቱን ለመጀመር እየተገደዱና የክትባቱን መድኃኒት ወደ ሀገራቸው በማስገባት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ