የኮሮናቫይረስ ምርመራ ያቋረጡ ዩኒቨርሲቲዎች የችግሩን አሳሳቢነት ተገንዝበው ምርመራ እንዲጀምሩ የአማራ ኀብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጠየቀ፡፡

103
የኮሮናቫይረስ ምርመራ ያቋረጡ ዩኒቨርሲቲዎች የችግሩን አሳሳቢነት ተገንዝበው ምርመራ እንዲጀምሩ የአማራ ኀብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጠየቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 05/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በኢንስቲትዩቱ የኀብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከል፣ መቆጣጠር፣ ምላሽ መስጠት እና መልሶ ማቋቋም ባለሙያ ተመስገን አንተየ በአማራ ክልል የኮሮናቫይረስ ምርመራ ሲያከናውኑ ከነበሩት 11 ተቋማት ውስጥ በዚህ ወቅት ደብረ ማርቆስ፣ እንጂባራ፣ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲዎች፣ ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ የአማራ ኀብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የኢንስቲትዩቱ ደሴ ቅርንጫፍ ምርመራ እያደረጉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ደብረታቦር ሆስፒታል፣ ጎንደር፣ ወሎ እና ወልድያ ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ ወደ መማር ማስተማር በመመለሳቸው እና ለቫይረሱ የተሰጠው ትኩረት ከመቀነሱ ጋር ተያይዞ ምርመራውን አቋርጠዋል፡፡
በሥራ ላይ የሚገኙት ተቋማትም ከማኀበረሰቡ የመመርመር ፋላጎት መቀነስ፣ የጤና ተቋማት ናሙና አወሳሰድ ዝቅተኛ መሆን እና የጤና ባለሙያዎች ከዚህ በፊት የሰሩበት ክፍያ ካለመከፈሉ ጋር ተያይዞ በሙሉ አቅማቸው ምርመራ እያከናወኑ አለመሆኑን ገልጸውልናል፡፡ በዚህም ከ300 እስከ 500 ሰዎች ብቻ ምርመራ እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ባለሙያው እንዳሉት የመመርመሪያ ማሽን ውድ መሆኑ እና የሰለጠነ ባለሙያ ባለመኖሩ ምክንያት ምርመራውን በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ ማድርግ ባይቻልም ሥራ ያቆሙ እና በሥራ ላይ የሚገኙ ተቋማት በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ እንዲገቡ በማድርግ እና ከሕብረተሰቡ የሚሰበሰበውን ናሙና አቅም ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ምርመራ ያቆሙ ተቋማትም የቫይረሱን ሥርጭት አሳሳቢነት ተረድተው እንደከዚህ ቀደሙ ለአካባቢያቸው ማኀበረሰብ የምርመራ አገልግሎት እንዲሰጡ ጠይቀዋል። ኢንስቲትዩቱም በየጊዜው ግፊት እያደረገ መሆኑን ነግረውናል፡፡
ስለ ኮሮናቫይረስ ማሕበረሰቡ ግንዛቤ ቢኖረውም ጥንቃቄ በማድርግ በኩል ችግር መኖሩንም ባለሙያው አንስተዋል፡፡ በዚህም በቫይረሱ የሚያዙት ሰዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ይገኛል፡፡ በአማራ ክልልም እስከ ሚያዝያ 3/2013 ዓ.ም ድረስ በቫይረሱ የተያዙት ሰዎች ቁጥር 9 ሺህ 57 መድረሱን ባለሙያው ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአጼ ቴዎድሮስን የታሪክ አሻራ ስፍራዎች የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የሚያስችል ፕሮጀክት አዘጋጀ።
Next articleእድሜአቸው የገፉ እና ተጓዳኝ ህመም ያለባቸው ዜጎች የኮሮና ቫይረስ ክትባትን እንዲወስዱ ተጠየቀ፡፡