“በተለያዩ አካባቢዎች በነዳጅ ማደያዎች እየተፈጠሩ ያሉ ሰልፎችን ለማስቀረት እየተሰራ ነው” የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

122
“በተለያዩ አካባቢዎች በነዳጅ ማደያዎች እየተፈጠሩ ያሉ ሰልፎችን ለማስቀረት እየተሰራ ነው” የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 04/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በመዲናዋ አዲስ አበባ ከተማ የነዳጅ ማደያዎች እየተፈጠሩ ያሉ ሰልፎችን በተመለከተ ከነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት ቁጥጥር ባለስልጣን እና የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት እንዲሁም ከነዳጅ ኩባንያ ማኀበራት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
በውይይቱም ወቅት የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል የሴክተሩን አደረጃጀት፣ መሠረተ ልማት፣ የአሠራር ስርዓት በመፈተሽ መስተካከል ያለባቸውን መመሪያዎችና ደንቦችን መነሻ በማድረግ እየተሰሩ ያሉ ጥናቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡
ጥናቶችን መሠረት በማድረግ ከነዳጅ ግዢ ስርዓት እስከ መጨረሻው ተጠቃሚዎች ድረስ በአቅርቦትና ጥራት ዙሪያ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
መንግስት የነዳጅ ማጓጓዣ ተሸከርካሪ ችግርን ለመፍታት በቂ ተሽከርካሪ ለማስገባት እየተሰራ ነው ያሉት ሚኒስትሩ በስራ ላይ ያሉትን ተሸከርካሪዎች በአግባቡ መጠቀምና ክትትል የምናደርግበት መንገድ ማስተካከል እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
ይሁን እንጂ አንዳንድ የነዳጅ ማደያዎችና ተጠቃሚዎች እጥረት እንዲፈጠር የሚያደረግ ተግባር እያከናወኑ መሆኑን በውይይቱ የተናሳ ሲሆን በቀጣይም የቁጥጥር ስርዓቱን በማሳደግ ወደ ተግባር ስለሚገባ የነዳጅ ማደያዎች ከመሰል ድርጊት እንዲቆጠቡ ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ዴፖዎች በቂ ክምችት ያላቸው በመሆኑ በአቅርቦት ላይ ምንም አይነት ስጋት እንደሌለ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ገልጿል።
በተለይም በመዲናዋ አዲስ አበባ ከተማ የነዳጅ ማደያዎች እየተፈጠሩ ያሉ ሰልፎችን ለመቅረፍ አዲስ አበባ ከተማ ከሚገኘው መጠባበቂያ ክምችት ዴፖ በማውጣት በከተማው ለሚገኙ ማደያዎች የተከፋፈለ መሆኑን ተገልጿል፡፡
የአቅርቦት ችግር ባለመኖሩ ሁሉም ህብረተሰብ ውድ ጊዜውን ሰውቶ አላስፈላጊ ስልፍ ከመፍጠር ተቆጥቦ ተረጋግቶ ስራውን እንዲቀጥል አቶ መላኩ ጥሪ ማቅረባቸውን ሚኒስቴር መስሪያቤቱ አስታውቋል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“የኮሮናቫይረስ ክትባት አቅርቦት ትምህርት፣ ባህልና ቱሪዝም ዘርፍን ታሳቢ ማድረግ አለበት” የትምህርት ሚኒስቴር
Next articleወርልድ ቪዥን በአማራ ክልል በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ተፈፃሚ የሚሆን ከ965 ሚሊዮን ብር በላይ የልማት ሥራዎች የስምምነት ሰነድ ተፈራረመ፡፡